አንዳንድ ሀገራት በሰዎች ተፈጥረዋል ከተባለ ከተፈጠረችው ሀገር አንዷ ኔዘርላንድስ ፈጣሪዎቹ ህዝቦች ደግሞ ኔዘርላንዳውያን ስለመሆናቸው ማንም አይጠራጠርም።
በሰሜን-ምዕራብ አውሮፓ የምትገኘውና ከትንሽነቷ የተነሳ በዓለም ካርታ ላይ በጉልህ የማትታየው ትንሿ ሀገር ኔዘርላንድ ባለፈው በአውሮፓውያኑ 2024 ውስጥ ብቻ ከ139 ቢሊየን ዶላር የሚበልጥ አጠቃላይ የግብርና ምርት ወደ ውጭ መላክ ችላለች።
በአፍሪካ በቆዳ ስፋት ሦስተኛ ከሆነችው ሱዳን 45 ጊዜ የምታንሰውና 41 ሺህ 543 ስኩየር ኪሎ ሜትር ብቻ የሚሆን መሬት ያላት ይህች አውሮፓዊት ሀገር እንዴት ከራሷ አልፋ ዓለምን መመገብ ጀመረች የሚለው እንቆቅልሽ ነው።
አብዛኛው ክፍሏ ከባሕር ጠለል በታች የሚገኝ በመሆኑ መሬቱ ከፍተኛ ውኃ የያዘና ረግረጋማ ነው። በዚህ ምክንያት ሀገሪቱ ለእርሻም ሆነ ለመኖሪያ ምቹ የሆነ በቂ መሬት አልነበራትም። ለዚህም ይመስላል ኔዘርላንድስ ውስጥ የሰው ልጅ መኖር አይችልም ይባል የነበረው።
ይሁን እንጂ ኔዘርላንድስ ይህንን መከራ የሚመስል ተፈጥሮ ወደ ዕድል በመለወጥ ከአሜሪካ ቀጥላ በዓለም ላይ ሁለተኛዋ ከፍተኛ የግብርና ምርት ላኪ ሀገር መሆን ችላለች።
ይህን አስገራሚ ስኬት ማግኘት የቻለችው ኔዘርላንድስ በታሪካዊው እና ሀገርበቀል በሆነው “ፖልደር” የተባለውን ዘዴ በመጠቀሟ ነው።
ኔዘርላንዳውያን ይህንን ተፈጥሮ የሰጠቻቸውን ረግረጋማ መሬት ለእርሻ እንደማይሆን በማሰብ ከመተው ይልቅ ሊታረስ ወደሚችል ለም መሬት ለመቀየር ያስችላል ያሉት ዘዴ ( ፖልደር ) በመሬቱ ውስጥ ያለውን ውሀ በማውጣት ረግራጋማነቱን ማስወገድ ነው የመረጡት።
ኔዘርላንዳውያን ይህንን ዘዴ ሲያስቡ በወቅቱ የውኃ መሳቢያ ዘመናዊ ፓምፖች ያልተፈጠሩበት ዘመን በመሆኑ በመሬቱ ውስጥ ያለውን ውኃ ወደላይ ስቦ ለማውጣት የንፋስ ወፍጮዎችን መትከል ነበረባቸው።
በዚህ ዘዴ ለእርሻ ያሰቡትን በንፋስ ወፍጮዎች አማካኝነት በመሬቱ ውስጥ ያለውን ውኃ በማውጣት መሬታቸውን የሚታረስ እና ለም ማድረግ ችለዋል።
ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ተስፋፍተው የውኃ መሳቢያ ፓምፖች ከመጡ በኋላም ይህንን ሥራ በመቀጠል ረግረጋማ መሬታቸውን ወደ ለም መሬት የመቀየሩን ሥራ ቀጥለውበታል።
ፈጠራና ብልሃትን ተጠቅመው ረግረጋማ ከሆነው መሬት ከ16-20 በመቶ የሚሆን የእርሻ መሬት በዚህ መልኩ ያገኙት ኔዘርላንዳውያን ሀገር በቀል በሆነው (በፖልደር) ዘዴ ሊታረስ የሚችል መሬት ለማግኘት ከፍተኛ የሰው ኃይል ጊዜ እና ገንዘብ ማውጣት ነበረባቸው።
አንዳንድ ሀገራት በሰዎች ተፈጥረዋል ከተባለ ከተፈጠረችው ሀገር አንዷ ኔዘርላንድስ ፈጣሪዎቹ ህዝቦች ደግሞ ኔዘርላንዳውያን ስለመሆናቸው ማንም አይጠራጠርም።
አሁን ላይ ኔዘርላንድ በፖልደር ዘዴ በተገኘው ውድ መሬት ላይ የላቀ የግብርና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከሌሎች ትላልቅ ሀገራት ተርታ በመሰለፍ ከዓለማችን የግብርና ምርቶች ላኪ ሀገራት መሀከል ከዋነኞቹ ተርታ መመደብ ችላለች።
ይህ የኔዘርላንድ ተሞክሮ የሀገር በቀል መፍትሄ የሰው ልጅ ፈጠራና የህዝቦች ትጋት ሲቀናጅ ምን ያህል ታላቅ ነገር መፍጠር እንደሚቻል የሚያሳይ ኅያው ምስክር ነው።
ታዲያ ከዝቅተኛው ቦታ ዳሎል እስከ ከፍታው ራስ ዳሽን በየአይነቱ መልከዓምድሩም አየር ንብረቱም ያለስስት የተሰጣት ኢትዮጵያ እንዴት አትበለጽግም? የመበልጸጊያ ጊዜስ አሁን አይደለምን?
ዋሲሁን ተስፋዬ