Search

ጎጠኛ ፍላጎትን ከሀገር ጥቅም በታች በመቅበር የጋራ እሴቶችን ማጉላት ይገባል

ሓሙስ ጥቅምት 13, 2018 79

ኢትዮጵያ በተለያዩ የፖለቲካ ትርክቶች ምክንያት ከፍተኛ ክፍፍል በገጠማት ወቅት፣ ሀገሪቱን የሚያስተሳስሩ በርካታ የወል እሴቶች እና ትርክቶች መኖራቸውን ምሁራን እና የሰላም ተሟጋቾች ያነሳሉ።
የታሪክ እና የፖለቲካ ምሁር ዓለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያውያን ለዘመናት ያቆዩት የጋራ መስተጋብር፣ ትግሎች እና ድሎች እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡
በሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የጋራ መስዋዕትነት ለሉዓላዊነት ከተደረጉ ትግሎች እና ድሎች መካከል የዓድዋ ድል ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለልማት፣ ለፍትሕ እና ለብልጽግና ባለው የጋራ ጥማት እና ፍላጎት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በሕብረት በመገንባት አሳይቷል ነው ያሉት፡፡
በርካታ የወል እሴቶች ያሏት ሀገር የጋራ ትርክት እንዳትገነባ ዋነኛ እንቅፋት የሆኑባት የተሻለ ነገዋን ማየት የፈሩ ጠላቶቿ መሆናቸውን ዓለማየሁ አረዳ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡
የኪንግስ ኦፍ ዓባይ ሚዲያ ሥራ አስኪያጅ እና የማህበረሰብ አንቂው ኡስታዝ ጀማል በሽር በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ እየተሰሩ ያሉ ፕሮጀክቶች በጋራ ዓላማ እና አንድነት ሲፈጸሙ የሚያስገኙትን አወንታዊ ውጤት መመልከት እየቻልን ነው ብለዋል፡፡
የወል ትርክቶችን በመገንባት ሀገሪቱን ከፍ ወደሚያደርጉ ሀሳቦች ማሳደግ ይገባል ያሉት ኡስታዝ ጀማል በሽር፤ ያለፉ ስህተቶችን ለመቀበል እና የጋራ ግቦችን ለመለየት ሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ስለመሆኑ ጠቁመዋል፡፡
የሀገሪቱን ፈተና የሚያበዙ የፖለቲካ ልሂቃንና የፖለቲካ መሪዎችም ጎጠኛ ፍላታቸውን ከሀገር ጥቅም በታች ቀብረው፣ የጋራ እሴቶችን የሚያጎሉ ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባቸው ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ የጋራ መግባባትና ፅኑ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚቻላት፣ የሚለያዩ ትርክቶችን ከማስተናገድ ይልቅ የሚያስተሳስሩ የጋራ እውነቶችን በአደባባይ በማንፀባረቅ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በሜሮን ንብረት