Search

የመደመር መንግሥት ፍልስፍና አቃፊ ትርክትን ማጉላት ነው - ዳግማዊ ተስፋዬ (ዶ/ር)

ሓሙስ ጥቅምት 13, 2018 44

የመደመር መንግሥት ፍልስፍና አቃፊ ትርክትን ማጉላት ነው ሲሉ የታሪክ መምህር እና ተመራማሪው ዳግማዊ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።
የቀደምት ስልጣኔ ባለቤት የነበረችውን ኢትዮጵያን ዳግም ወደ ክብሯ ለመመለስ መፍትሄው አቃፊ የሆነ የወል ትርክት ነው ብሎ የመደመር መንግሥት ያምናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ያሳለፈቻቸው የእርስ በርስ ጦርነቶች እና የፖለቲካ አለመረጋጋቶች ለዕድገቷ ማነቆ እንደነበሩም አንስተዋል።
ሀገሪቱ የነበሯትን ታላላቅ ስልጣኔዎች ለማስቀጠል የሚያስችላትን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መዋቅር እንዳትፈጥር ከፋፋይ ትርክቶች ወደ ኋላ አስቀርተዋታል ብለዋል።
በቀይ ባሕር የአዳዲስ የፖለቲካ ኃይሎች ብቅ ማለት፣ የንግድ እንቅስቃሴዎች አቅጣጫ እና የኃይል ሚዛን መቀየር ሀገሪቱ በወጥነት የገነባችውን ስልጣኔ ማስቀጠል እንዳትችል ያደረጓት ዋና ዋና ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በአጠቃላይ ከፋፋይ ትርክቶች እና አግላይ የፖለቲካ ሥርዓቶች ሀገሪቱን ወደኋላ አስቀርቷቷል ነው ያሉት።
ከተለመደው አሠራር በመውጣት ችግሮችን በሳይንሳዊ መንገድ ለመፍታት የመደመር መንግሥት የተለመው ሀገራዊ ትርክትን የማጉላት ፍልስፍና ሁነኛ መፍትሄ ነው ብለዋል።
የመደመር መንግሥት በተለያዩ አካላት የሚነሱ ጥያቄዎችን በመመርመር እና ችግሮቹን ሊፈቱ የሚችሉ አቃፊ ትርክቶችን በማጉላት ኢትዮጵያን ወደ ስልጣኔ ለማሻገር እየሠራ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የመደመር መንግሥት ፍልስፍና ሲነሱ የነበሩ ተበደልኩ፣ ተገለልኩ፣ እኩል አልተስተናገድኩም የሚለውን የማኅበረሰቦች ቅሬታ የመለሰ እሳቤ ነው ብለዋል።
አክለውም፥ የተባበረ ክንድ ያሸንፋል የሚለውን የመደመር መንግሥት ፍልስፍና በጋራ ተግብረን ለልጆቻችን የተሻለች ሀገር ለማስተላለፍ ቆርጠን መነሳት ይገባናል ነው ያሉት።
በሄለን ተስፋዬ