በተባበሩ ክንዶች በመደመር የከበረ እሳቤ መሥራት በዓለም ፊት ሁሉ አንደኛ የመሆን ቀጥተኛው ጎዳና ለመሆኑ አረንጓዴ ዐሻራችን የሚታይ የሚጨበጥ ምስክር ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የምስራቅ ኢትዮጵያ ጌጥ፣ የብዙኃን መናኸሪያ እና የእንግዳ ተቀባይ ሕዝብ ምድር" ሲሉ በገለጿት በጅግጅጋ ከተማ አረንጓዴ ዐሻራቸውን ማኖራቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው አስታውቀዋል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ሙሁመድ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችም በተከላው ተሳትፈዋል።
"በመትከል ማንሰራራት" በሚል መርህ ዛሬ በ7ኛ ዓመት 700 ሚሊዮን ችግኞች በአንድ ጀምበር እየተተከሉ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአረንጓዴ ዐሻራ እስከ 2018 ዓ.ም 50 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ ስለመሆኑም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ልጆች ሁሉ በዚህ ሃገራዊ የልማት ሰልፍ ላይ ናቸው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን፤ ከእቅዱ ውስጥ እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ 46 ቢሊዮን ችግኞች መተከላቸውን ገልጸዋል።
በጅግጅጋም ሆነ በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች የምንተገብረው አረንጓዴ ዐሻራ የሃገራዊ ተግባሩ ተደማሪ፣ ከአካባቢው ውበት የሚሻገር፣ በኢኮኖሚ የሚመነዘር፤ የኑሮ መሰረት እና ኃብት ከሆኑ ነባራዊ እሴቶችም ጋር ሰም እና ፈትል ሆኖ የሚስማማ የታሪክ ማህተማችን ነው።
የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ ፕሮግራም በዓለም ላይ ትልቁ የአረንጓዴ ልማት ትግበራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተባበሩ ክንዶች በመደመር የከበረ እሳቤ መሥራት በዓለም ፊት ሁሉ አንደኛ የመሆን ቀጥተኛው ጎዳና ለመሆኑ አረንጓዴ ዐሻራችን የሚታይ የሚጨበጥ ምስክር ነው ብለዋል።