የጦርነት ሥጋትን ለመከላከል አስቀድሞ ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ ነገር መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመደመር መንግሥት መጽሐፍ አጽንኦት ይሰጣል።
ስለወታደራዊ ዝግጅት አስፈላጊነት የሚያወሳው መጽሐፉ ገፅ 72 ላይ፥ በተለይ ባለንበት ዓለም ውስጥ የሀገር መከላከያ መገንባት ሌላ አማራጭ የሌለው ተግባር ነው፤ የመከላከል ዐቅም ግን በአንድ ጀምበር የሚገነባ አይደለም ይላል።
መከላከያ ሠራዊት መገንባት ደግሞ እጅግ ከፍተኛ ሙዓለ ንዋይ የሚፈልግ ሀገራዊ ተልዕኮ ነው የሚለው የመደመር መንግሥት መጽሐፍ፤ በየጊዜው ወታደራዊ ዘመናዊነትን እና ተወዳዳሪነትን እያካበቱ የመሄድ ተግባር መሆኑን ያነሳል።
ዓለም ከደረሰበት የውትድርና ትጥቅ ደረጃ መድረስ ያስፈልጋል የሚለው መጽሐፉ፤ በተለይም ሥጋቶቻችንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ጦርነትን የሚያስቀር የትጥቅና የሠራዊት ዝግጅት ማድረግ ለነገ የሚባል እንዳልሆነ በግልፅ አስቀምጧል።
ጦርነት ገና ግም ሳይል፣ በሥጋት ብቻ ዓለም ብዙ ሀብቷን እንድትገብርለት አድርጓል፤ ጦርነት ድምፁ ሳይሰማ ብዙ የሚዘርፍ ኃያል ነው፤ በሌሎች ልማቶች ላይ መዋል የሚችል ሀብትን ሲወስድ ቅር አይለውም ሲልም ያስረዳል።
የሀገራችን ታሪክ ከጦርነት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ በሰላሙም ጊዜ የመከላከያ ሠራዊት ግንባታዋን አጠናክራ የመቀጠል ግዴታ ውስጥ ገብታለች ሲልም የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ይገልጻል።
በጌትነት ተስፋማርያም