የአውሮፓ ሕብረት የበካይ ጋዝ ልቀትን በመቀነስ በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ መድረኮች መሪ መሆን እንዳለበት የሕብረቱ ፓርላማ አባላት ጠይቀዋል።
ጥሪው የቀረበው ፓርላማው በሚቀጥለው ወር በብራዚል አስተናጋጅነት ለሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ኮንፈረንስ (ኮፕ30) ትኩረት ሰጥቶ የሚያቀርባቸውን ጉዳዮች ይፋ በአደረገበት ወቅት ነው።
የአውሮፓ ሕብረት የአካባቢ፣ የአየር ንብረት እና የመድኃኒት ደህንነት ኮሚቴ ባቀረበው የምክረ ሀሳብ፣ የሕብረቱ አባል ሀገራት በካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ግብ እንዲያስቀምጡ፣ በነዳጅ ላይ ያላቸውን ጥገኝነትና ለነዳጅ የሚሰጡትን ድጎማ እንዲቀንሱ እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ የሚሰጡትን የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያሳድጉ ተጠይቋል።
የኮፕ 30 ዓላማ የዓለም አማካይ የሙቀት መጠን ከ1.5 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንዳይጨምር ለማድረግ ሀገራት የሚሰጡትን የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያሳድጉ ማበረታታት መሆኑም ተገልጿል።
የፓርላማ አባላቱ ሁሉም የሕብረቱ አባል ሀገራት ለአዳጊ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በቂ የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
በላሉ ኢታላ