Search

ሳይገባን ገብተን ዋጋ የከፈልንበት መንገድ እና አሁን የመረጥነው የራሳችን ጎዳና

ዓርብ ጥቅምት 14, 2018 2539

የሰው ልጅ በዘመናዊ የአስተዳደር ሥርዓት መመራት ከጀመረ ወዲህ ዓለም ካስተናገደችው የርዕዮተ ዓለም ፍትጊያዎች በላይ ውጥንቅጧን ያወጣት ጉዳይ አልታየም። መመራት ያለብን በዚህኛው ስርዓት ነው አይደለም በዚያኛው ነው በሚሉ ጎራዎች ተከፍሎ ዓለም ውዱን ዋጋ ከፍላለች።

በሊበራሊዝም እና ሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለሞች መካከል የተካሄደውን ፍትጊያን ያህል ደግሞ በየትኞቹም ርዕዮተ ዓለሞች መካከል አልተደረገም። አውዳሚውን የጦር መሳሪያ አሰርቷል የሰው ልጅ በጦር መሳሪያ እሽቅድምድም ውስጥ ገብቶ ለመጠፋፋት ብዙ ተግቷል። ዓለም በታሪኳም የመዘገበችው የመጠፋፋት ዘመን ብዙ ምክንያቶቹ ቢኖሩትም ዋናው ግን ርዕዮተ ዓለማዊ መሆኑን ከዓለም ጦርነቶች መመልከት ይቻላል።

ሊበራሊዝም የሰው ልጅ በነጻነት መኖር አለበት የሚል እሳቤን ይዞ የሚንቀሳቀስ በመሆኑ በተለይ የመናገር እና የሃይማኖት ነፃነት ያሉ የሲቪል ነፃነቶችን በመጠበቅ በኢኮኖሚውም ረገድ የመንግሥትን ሚና ውስን ማድረግ ዋና ዓላማው ነው

እንደ ጆን ሎክ፣ አዳም ስሚዝ፣ ጆን ስቱዋርት ሚል አይነት የርዕዮተ ዓለሙ ቁልፍ አቀንቃኞች ፍልስፍናዊ መልኩን ለዓለም ሲያስተዋውቁ የእንግሊዟ ማርጋሬት ታቸር እና 40ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሮናልድ ሬገን ፖለቲካዊ መልኩን ለዓለም ከማስተዋወቅ ጀምሮ ካፒታሊዝምን የተለየ ከፍታ ላይ በማድረስ ይታወሳሉ፡፡ 

በተቃራኒው በካርል ማርክስ እና ፌሬድሪክ ኤንግልስ የተፈጠረው ሶሻሊዝም የሠራተኛው እና የኢንዱስትሪ መደቦችን በመፍጠር ለሠራተኛው የሚቆም ርዕዮተ ዓለም ነው፡፡ ይህም በኢንዱስትሪዎች ምክንያት ለተፈጠሩ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መዛባት ምላሽ ለመስጠት እንደተፈጠረ ይጠቀሳል። ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን ለማሳካት የማምረቻ ዘዴዎችን የጋራ ወይም የሕዝብ ባለቤትነት ይደግፋል።

ዓላማውን ለማሳካት የሚመራውም በሥር ነቀል ለውጥ (አብዮት) ነው። የኮሚኒዝም ታሪካዊ ትግል በዋነኛነት ከካፒታሊዝም ጋር ሲሆን፣ ይህ ትግልም በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ለተፈጠረው የሁለት ዋልታዎች ፍጥጫ ምክንያት ሆኗል።

ቀዝቃዛው ጦርነት የሶቪየት ኅብረት መንግስት-ሶሻሊስት ሞዴልን ከምዕራቡ ዓለም ካፒታሊስት ጋር በማፋጠጥ ዓለምን ከፍተኛ ስጋት ውስጥ የከተተው ፍጥጫ የሚታወስ ነው። የእነዚህ ሁለት የሃያልነት ማረጋገጫ ፍላጎት ጀርመንን በግንብ ከፍሏል፣ ኮሪያን ሁለት ሀገር አድርጓል። በኋላ ላይም ሶቭየት ኅብረትን ወደትናንሽ ሀገራት የከፋፈለ ታሪካዊ ክስተት እንዲፈጠር አድርጓል።

በእርግጥ ሁለቱ ርዕዮተ ዓለሞች የእነሱን ጎራ በተቀላቀሉ ሀገራት ውስጥ የውክልና ጦርነት እስከማካሄድም ደርሶ ዓለምን ለቀውስ ዳርጓል። ኢትዮጵያም የዚያ ጽዋ ቀማሽ ሆና ነበር፡፡ በሶቪየት ኅብረት የሚመራው የሶሻሊዝም ካምፕ ከኅብረቱ መበተን ጋር የተዳከመ ቢሆንም፣ ርዕዮተ ዓለሙ ግን በበርካታ ሀገራት ላይ ከፍተኛ የፖሊሲ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡

ኢትዮጵያ ዋጋ የከፈለችበት የርዕዮተ ዓለም ዥዋዥዌ

ኢትዮጵያ በአጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የተተነተነ ርዕዮተ ዓለም ባይኖራትም በተግባር ግን ከምዕራባውያኑ በተለይም ከአሜሪካ ጋር ወዳጅ ስለነበረች የካፒታሊዝሙ ካምፕ ውስጥ እንደነበረች መገመት ይቻላል፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በርካታ ተቋማት የተገነቡት በአሜሪካ ድጋፍ ጭምር ነበር።

በዲፕሎማሲው በኩል ግን ኢትዮጵያ ከምሥራቁም ሆነ ከምዕራቡ ወገን ጋር መልካም ግንኙነትን መመሥረት በመቻሏ እና የሁለቱንም ጎራ ወዳጅነት በጥንቃቄ በመያዟ ፍትጊያ ውስጥ ሳትገባ ቆይታለች፡፡

ወታደራዊ ደርግ ወደ ሥልጣን ሲመጣ "የቡርዧ ሥርዓት" ያለውን ባላባት ለመታገል የሚያስችለውን መደብ ለመፍጠር የሶሻሊዝም ካምፕን ተቀላቀለች፡፡ ኢትዮጵያ ይህን ካምፕ መቀላቀሏ ብቻ ሳይሆን ካፒታሊዝም መሩን የምዕራብ ዓለም የመደብ ጠላት አድርጋ መፈረጇ ደግሞ አሜሪካ መሩ የካፒታሊዝም ካምፕ ኢትዮጵያን ከሶቭየት ኅበረት እኩል በጠላትነት እንዲፈርጃት አደረገ፡፡

በእርግጥ ኢትዮጵያ ሶሻሊዝምን ተቀብላ ሥራ ስትጀምር ስለርዕዮተ ዓለሙ ሰፊ ዕውቀት ኖሮ ሳይሆን በወቅቱ እንደፋሽን ጭምር ይታይ ስለነበር ጉዳዩን ብዙ ለመመርመር ጊዜ አልተሰጠውም። በወጣቶች ዘንድ በስፋት ይታይ የነበርው የሶሻሊዝም እንቅስቃሴን ሀገርም በፍጥነት ስትገባበት ጥቅም እና ጉዳቱን ለማገናዘብ እድል አልተገኘም።

በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ተገድዳ ወደ ምሥራቁ ጦርነት በገባች ጊዜ ቀድሞ በራሷ ገንዘብ የገዛችውን የጦር መሣሪያ እንኳን የወቅቱ የአሜሪከ ፕሬዚዳንት በነበሩት ጂሚ ካርተር ተከለከለች፡፡ በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት እያሽቆለቆለ መሆኑን የተረዱት አሜሪካውያንም ፊታችውን ከደርግ መንግሥት ለማዞር ተገደዱ።

በኦጋዴን ጦርነት ወቅት አሜሪካ ድጋፏን ከኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ በማዛወር አፍሪካ ቀንድ ቀዝቃዛው ጦርነት አካል እንዲሆን አድርጋለች። ይህ ያልተጠና የርዕዮተ ዓለም አቀዳድ ኢትዮጵያ ባለፉት 50 እና 60 ዓመታት ለመጣችበት ውጥንቅጥ ምክንያት ሆኖ ውድ ዋጋም አስከፍሏታል፤ የልጆቿንም ደም አፋሷል፡፡

ኢትዮጵያን አርነት ያወጣው መደመር

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በመደመር መንግሥት መጽሐፋቸው እንደጠቀሱት "የመደመር ፍልስፍና የሀገራችን መሰረታዊ ችግር የአስተሳሰብ ችግር ነው ብሎ ያምናል"፡፡ ርዕዮቱን እውን ለማድረግም የሚከተለው መንገድም፣ አቃፊነትን ነው፡፡

መደመር የመንግሥት ሚና እንደ ካፒታሊዝሙ የዳር ተመልካች፣ እንደ ሶሻሊዝሙም ሁሉንም ነገር መጠቅለል አለበት የሚል እንዳልሆነ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ በኢኮኖሚው ግንባታ የመደመር መንግሥት ሚና በአንድ በኩል የራሱን ሚና እየተወጣ ሚዛንን መጠበቅ ነው፡፡ በፖለቲካል ኢኮኖሚው ውስጥ ሚና የሚጫወቱ አካላትን በመደገፍ እና በማብቃት ወሳኝ ሚና እንዲጫወቱ ማስቻል ነው፡፡

በመደመር መጽሐፍ ላይ እንደተጠቀሰው ኢትዮጵያ የርዕዮተ ዓለም እስረኛ መሆኗ ዋጋ አስከፍሏታል፡፡ ርዕዮተ ዓለሞቹ መውሰድ ቢያስፈልግ እንኳን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማሰናሰል መሆን እንደነበረበት ነው መደመር የሚያትተው፡፡መደመር አፍርሶ የሚጀምር ሳይሆን ከትላንት ወረትን ወስዶ ዛሬን የሚሠራ፣ ለነገው ደግሞ ጥሪትን የሚያስቀምጥ እሳቤ ነው፡፡

መደመር የትኛውም የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም አይጠቅምም የሚልም ሆነ እንዱ ርዕዮተ ዓለም ፍጹም ነው የሚል አቋም የለውም፤ ይልቁንም ከሁሉም የተሻለውን ሀሳብ ለመውሰድ እና ወደ ኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ለመመንዘር ዘግጁ ነው፤ ራሱም ቢሆን ሀሳብን ተቀብሎ ለመሻሻል ዝግጁ ነው፡፡

የመደመር እሳቤ መተባበር ለኢትዮጵያ ኅብረብሔራዊ አንድነት፣ ሰላም እና ልማት መሥራትን የሚደግፍ እንጂ ፍረጃን የሚከተል አይደለም። የትኛውም ሀሳብ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ከሆነ ለማካተት ዝግጁም ነው፡፡ ፉክክር እና ትብብር ለጤናማ ማኅበረሰብ አስፈላጊ ናቸው ይላል፤ ሰዎች፣ ቡድኖች እና ተቋማት ለጋራ ግቦች በመተባበር ለላቀ ደረጃ የሚወዳደሩበት "መካከለኛ መንገድ" መኖሩን፣ ይህም የተቀናጀ ውጤት ይፈጥራል ይላል።

የኢትዮጵያን ታሪካዊ እና ባህላዊ እሴቶች በመመርኮዝ ለኢትዮጵያ ልዩ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ተግዳሮቶች በሀገር በቀል መፍትሄዎችን አዘጋጅቷል። ኢትዮጵያ ድህነትን እና የፖለቲካ አለመረጋጋትን አልፋ ወደ ብልፅግና እንድትሸጋገር ለግል እና ቡድን ጥቅም ከመሥራት ወጥተን ለጋራ ብሔራዊ ጥቅም ወደመሥራት እንድንመጣ ጥሪ ያቀርባል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንደሚጠቅሱት መንግሥታቸው በመደመር መርህ በፈጠረው አደጋን የመቋቋም (Shock absorbers) አቅሙን ተጠቅሞም ከውጭ እና ከውስጥ የተጋረጡበትን ፈተናዎች እያለፈ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የተረጋጋ እና ተከታታይ ዕድገት እንዲያስመዘግብ አስችሏል፡፡

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ፖሊሲው ኢትዮጵያ ያላትን አቅም ሙሉ ተጠቅማ ለማደግ የሚያስችላትን መንገድ ተከትሎ ከስንዴ ልመና ወደ ስንዴ አምራችነት አሸጋግሯታል፡፡ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ተጀምሮ የተጓተቱትን ጨምሮ በርካት ሜጋ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት እና በጥራት የመፈጸም አቅም ፈጥሯል፡፡ 

በለሚ ታደሰ