የበርካታ ፀጋዎች ባለቤት የሆነችው አፍሪካ ያሏትን ፀጋዎች በመጠቀም እንድታድግ አፍሪካውያን በጋራ ልንሰራ ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ፡፡
11ኛው የጣና ፎረም "አፍሪካ በተለዋዋጩ የዓለም ሥርዓት" በሚል መሪ ሀሳብ በባሕር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፤ የጣና ፎረም የአፍሪካ ችግሮችን በአፍሪካውያን ለመፍታት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
አህጉሪቱ የሚገጥሟትን የሰላምና ደህንነት ችግሮች በጋራና በዘላቂነት በመፍታት፣ ደህነነቷ የተጠበቀ አህጉር መገንባት ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።
ለዚሁ ደግሞ የጣና ፎረም የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑ ነው የገለፁት።
የባሕር ዳር ፍፁም ሰላማዊ፣ ልማቷን እያፋጠነች የምትገኝ፣ ለጉብኝት እና የተለያዩ ኮንፈረንሶች ለማካሄድ ተመራጭ ከተማ መሆኗን ገልፀው፤ ለዚህም የጣና ፎረም በከተማዋ መካሄዱ ማሳያ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በከተማዋ ዛሬ በጀመረው ፎረም በአፍሪካ ቀንድ የሰላም እና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ ውይዮቶች ይካሄዳሉ።
በፎረሙ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጢሞትዮስ (ዶ/ር) ጨምሮ የተለያዩ አፍሪካ ሀገራት ልዑካን፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት ተወካዮች እንዲሁም ዲፕሎማቶች እየተሳተፉ ነው፡፡
ፎረሙ ከነገ ጀምሮ ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ የሚካሄድ ይሆናል።
በሳሙኤል ወርቃየሁ