በአሁኑ ወቅት በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው ግጭትና ተከትሎት የመጣው የሆርሙዝ ወሽመጥ በከፊል መዘጋት፣ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ ላይ ከፍተኛ አለመረጋጋት ፈጥሯል።
ይህ ቀውስ የነዳጅ ዋጋ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአንድ በርሜል ከ70 ዶላር ወደ 140 ዶላር እንዲያሻቅብ በማድረጉ፣ ሀገራት የነዳጅ አጠቃቀማቸውን በአዲስ መልክ እንዲፈትሹ አስገድዷቸዋል።
ኢትዮጵያም የዚሁ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ አካልና በቀውሱ ቀጣና አቅራቢያ የምትገኝ በመሆኗ፣ የችግሩ ቀጥተኛ ተጽዕኖ አርፎባታል።
ይሁን እንጂ ሀገራችን እንዲህ ያሉ ዓለም አቀፍ ቀውሶችን አስቀድማ በመረዳት የጀመረችው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታና የታዳሽ ኃይል ልማት፣ በአሁኑ ወቅት ለተከሰተው ቀውስ እንደ ትልቅ የመከላከያ ጋሻ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በዚህ ወቅታዊ ቀውስ ዙሪያ ባስተላለፉት መመሪያ፣ ኢትዮጵያ ያላትን ውስን የነዳጅ ሀብት በቁጠባና ለታለመለት ዓላማ ብቻ መጠቀም እንዳለባት አሳስበዋል። ችግሩ ተፈትቶ የነዳጅ አቅርቦት ሥርዓቱ ወደነበረበት እስኪመለስ ድረስ፣ ነዳጅን በቁጠባ መጠቀምና ለመሠረታዊ አገልግሎቶች ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባም አቅጣጫ አስቀምጠዋል። ይህ ጥሪ መንግሥት ነዳጅን ለትራንስፖርት፣ ለጤና እና ለምግብ አቅርቦት ቅድሚያ እንዲውል ከሰጠው መመሪያ ጋር ፍጹም የተጣጣመ ነው።
ኢትዮጵያ ከነዳጅ ጥገኝነት ለመውጣት የጀመረችው ትልቁ እንቅስቃሴ በ2016 ዓ.ም የነዳጅ ተሽከርካሪዎች ወደ ሀገር እንዳይገቡ በማገድ የወሰነችው ታሪካዊ ውሳኔ ነው። ይህ ውሳኔ በወቅቱ ብዙዎችን ቢያስገርምም፣ አሁን ላለው የነዳጅ ቀውስ አርቆ አሳቢና ብልህ እርምጃ መሆኑ በተግባር ተረጋግጧል።
እስከ የካቲት 2018 ዓ.ም ድረስ ባለው መረጃ መሠረት፣ በኢትዮጵያ መንገዶች ላይ የሚንቀሳቀሱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ከ100 ሺህ በላይ ደርሷል። ይህም ከጠቅላላው የተሽከርካሪ ገበያ የ6 በመቶ ድርሻ እንዲኖራቸው አድርጓል። ይህ ሽግግር ሀገራችን በየዓመቱ ለነዳጅ ግዥ የምታወጣውን ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሬ ለመታደግና የኃይል ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወተ ነው።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለዚህ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ሽግግርና ለኢንዱስትሪ ልማት ዋነኛው የኃይል ምንጭ ነው። ግድቡ የኢትዮጵያውያን ኩራት ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን የታዳሽ ኃይል ትብብር በተግባር የተገለጠበት ማሳያ ነው።
ከሃይድሮ ፓወር በተጨማሪ፣ በቅርቡ በሶማሌ ክልል የተመረቀው የ120 ሜጋዋት የአይሻ 2 የነፋስ ኃይል ማመንጫን ጨምሮ የፀሐይና የጂኦተርማል ኃይል ምንጮችን በማስፋፋት ኢትዮጵያ የኃይል ድብልቅ (Energy Mix) ሥርዓቷን እያጠናከረች ትገኛለች።
የኢትዮጵያ የታዳሽ ኃይል ጉዞ፣ ከዓለም አቀፍ የነዳጅ ቀውስ ስጋት ነፃ የሆነችና በራሷ አቅም የምትመራ ሀገር ለመገንባት የተነደፈ ስኬት ነው። ይህም በመደመር መንግሥት እሳቤና በሀገር በቀል ኢኮኖሚ ፍልስፍና፤ የመንግሥት፣ የሕዝብና የተፈጥሮ ሀብትን በማቀናጀት ለዘላቂ ብልጽግና መሠረት እየተጣለ መሆኑን ያሳያል።
በለሚ ታደሰ