ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የዘራችው ዘር ዛሬ ፍሬ አፍርቶ፣ አገራዊ ብቻ ሳይሆን ቀጠናዊ ፋይዳውም ጎልቶ መታየት ጀምሯል።
የኢትዮጵያ ደን ልማት ባወጣው መረጃ መሠረት፤ የአገሪቱ የደን ሽፋን እያደገ መምጣቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለታችኛው ተፋሰስ አገራትም ትልቅ እፎይታ ሆኗል።
መጋቢት 12 ቀን 2018 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ14ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም የደን ቀን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የኢትዮጵያ ደን ልማት ዋና ዳይሬክተር አቶ ከበደ ይማም፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት የታየው ለውጥ አስደናቂ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ያላት የደን ሽፋን የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ያላቸውን የጎርፍ ተጋላጭነት 15 በመቶ መቀነስ አስችሏል ሲሉ ተናግረዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ከሰባት ዓመታት በፊት 17 ነጥብ 2 በመቶ ብቻ የነበረው የአገሪቱ የደን ሽፋን፤ ዛሬ ላይ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ብሏል።
ዘንድሮ "ደን ለኢኮኖሚ" በሚል መሪ ቃል የሚከበረው የዓለም የደን ቀን፤ ኢትዮጵያ በዘርፉ ያስመዘገበችውን ስኬት ከማጉላት ባለፈ፣ የባለድርሻ አካላትን ቅንጅት በማጠናከር ለላቀ ውጤት የሚመከርበት መድረክ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሥጋት የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ ለመከላከል በምታደርገው ጥረትም የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብርን እንደ ዋነኛ ማሳያ በማቅረብ ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተጫወተች ትገኛለች።
በቢኒያም ወንድይፍራው