Search

ከወታደራዊ ፍጥጫ ወደ ዓለም አቀፍ የኢነርጂ ጦርነት የተሸጋገረው የመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት

ሓሙስ መጋቢት 10, 2018 121

የመካከለኛው ምሥራቅ ቀውስ ባለፉት 12 ሰዓታት ውስጥ ወደ አዲስ እና አደገኛ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።
በአሜሪካ እና በእስራኤል የሚመራው "ኦፕሬሽን ኤፒክ ፊውሪ" ሦስተኛ ሳምንቱን በያዘበት በዚህ ወቅት፣ ግጭቱ ከቀጥታ ወታደራዊ ዒላማዎች አልፎ የዓለምን የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ወደሆኑት የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ መሠረተ ልማቶች ዘልቋል።
እስራኤል የኢራንን የኢኮኖሚ አቅም ለማዳከም በወሰደችው ስልታዊ እርምጃ፣ በመጋቢት 18 ቀን በኢራን ግዙፍ የጋዝ ክምችት በሆነው ‘ደቡብ ፓርስ’ ላይ የአየር ጥቃት ፈጽማለች።
ይህ እርምጃ የኢራንን የኃይል አማራጮች ስልታዊ በሆነ መንገድ የመምታት እና ሀገሪቱን የኃይል ሉዓላዊነት የማሳጣት እንቅስቃሴ አካል ተደርጎ ይወሰዳል።
ኢራን በእስራኤል ለተፈጸመባት ጥቃት በሰጠችው ምላሽ፣ ጥቃቱን ወደ ባህረ ሰላጤው ሀገራት አስፋፍታለች። በዚህም በዓለም ግዙፉ የተፈጥሮ ጋዝ ማዕከል በሆነው የኳታር ራስ ላፋን ላይ ጥቃት የሰነዘረች ሲሆን፣ በተመሳሳይ ሁኔታ በሳውዲ ዓረቢያ የሚገኙ የኃይል ማመንጫና ማጣሪያ ጣቢያዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች መፈጸማቸው ተዘግቧል። ይህም ኢራን "እኔ የኃይል ዋስትና ካጣሁ፣ ቀጣናውም አያገኝም" የሚል መልዕክት እያስተላለፈች መሆኑን ያሳያል።
ዶሃ በራስ ላፋን ላይ የደረሰውን ከፍተኛ የንብረት ውድመት ተከትሎ፣ በሀገሪቱ የሚገኙ የኢራን የደኅንነት እና የወታደራዊ አባላት በአስቸኳይ ሀገር ለቀው እንዲወጡ ወስናለች።
የደኅንነት ባለሥልጣኗን አሊ ላሪጃኒን ግድያ ተከትሎ፣ ኢራን በቴል አቪቭ ላይ በትንንሽ ቦምቦች የሚከፋፈሉ ሚሳዔሎችን ተኩሳለች። ይህ ዓይነቱ ጥቃት በተለይ ሰፊ ቦታን በማዳረስ እና መከላከያዎችን በመጥለፍ ረገድ አስቸጋሪ በመሆኑ የእስራኤልን የደኅንነት ስጋት ከፍ አድርጎታል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ እስራኤል በኢራን የጋዝ መሬት ላይ ጥቃት እንደምትፈጽም አሜሪካ አስቀድማ የምታውቀው ነገር እንዳልነበረ ገልጸዋል። ሆኖም ድርጊቱ "በኃይል የተሞላ እርምጃ" እንደነበረ እና በቀጣይ ኢራን ጥቃት ካልሰነዘረች በቀር እንዲህ ዓይነት እርምጃ ዳግም እንደማይፈጸም መናገራቸው የዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችን አቅጣጫ ጠቋሚ ነው።
ይህ የጥቃት አቅጣጫ የሚከተሉትን ሦስት ዋና ዋና ስልታዊ አንድምታዎች ይዟል፦
ጦርነቱ ከፊት ለፊት ግንባር ወደ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንቶች መሸጋገሩ፣ ሀገራት በቀላሉ ሊያገግሙ የማይችሉትን ጉዳት እያስተናገዱ መሆኑን ያሳያል። የነዳጅ ማጣሪያዎች እና የጋዝ መስኮች መመታት የረጅም ጊዜ የጥገና እና የፋይናንስ ጫናን ያስከትላል።
ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ኳታር እና ኢራን በዓለም የኢነርጂ አቅርቦት ውስጥ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ፣ በእነዚህ ሀገራት ተቋማት ላይ የሚሰነዘር ጥቃት በቀጥታ በዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ላይ ንረት ያስከትላል። ይህ ደግሞ በኢነርጂ ላይ ጥገኛ የሆኑ ሀገራትን (እንደ ኢትዮጵያ ያሉ) ማክሮ-ኢኮኖሚን በቀጥታ ይፈታተናል።
ግጭቱ በሁለት ሀገራት መካከል ብቻ ሳይሆን፣ መላውን ባህረ ሰላጤ እየሳበ መሆኑ ቀጠናዊ ደኅንነትን አደጋ ላይ ጥሎታል።
በመሠረተ ልማት እና በኢነርጂ ጣቢያዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ዓለም አቀፍ የንግድ እና የሎጂስቲክስ መስመሮችን የማነቅ አቅም አላቸው።
በለሚ ታደሰ