Search

የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ፦ የታሪክ ስህተቶች እና የአምባሳደር ኸርማን ኮኸን ምስክርነት

ሓሙስ መጋቢት 10, 2018 218

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ጂኦ-ፖለቲካዊ ሚና እና የኢኮኖሚ ጥንካሬ ለማስቀጠል የባሕር በር ጉዳይ የቅንጦት ሳይሆን የሕልውና ጥያቄ መሆኑ የታመነ እውነት ነው።

ሀገራችን በአሁኑ ወቅት የባሕር በር ባለቤት አለመሆኗ ለወደብ ኪራይና ለትራንዚት የምታወጣው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለሁለንተናዊ ዕድገቷ እንቅፋት ሆኖ ቀጥሏል።

ይህ ትልቅ ሀገራዊ አጀንዳ የሆነው የባሕር በር ጥያቄ መነሻው ግንቦት 1983 . በለንደን ኮንፈረንስ ወቅት የተፈጠሩ ዲፕሎማሲያዊ ስህተቶች እና የወቅቱ መሪዎች የነበራቸው የተሳሳተ አቋም እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያረጋግጣሉ።

በተለይም የወቅቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ረዳት የነበሩት አምባሳደር ኸርማን ኮኸን ያቀረቡት የባሕር በር መብትን የማስከበር አማራጭ ሐሳብ በወቅቱ የነበሩት የኢሕአዴግ መሪዎች ውድቅ ማድረጋቸው ለዛሬው ችግር ዋነኛው ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል።

በለንደን በተካሄደው የሰላም ኮንፈረንስ ወቅት አምባሳደር ኸርማን ኮኸን ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በፖለቲካ ቢለያዩም በኢኮኖሚ ግን አንድ ሆነው እንዲቀጥሉ የሚያስችል የጋራ የኢኮኖሚ ኅብረት እንዲመሰረት ሐሳብ አቅርበው እንደነበር ከዚያ በኋላ ባደረጓቸው ቃለ መጠይቆች ጠቅሰዋል።

የአምባሳደሩ ሐሳብ ኤርትራ ነጻ ሀገር ብትሆንም ኢትዮጵያ የአሰብን ወደብ እንደራሷ ወደብ የምትጠቀምበት እና ሁለቱ ሀገራት የጋራ ገንዘብ እና የንግድ ቀጣና የሚኖራቸው ውቅር እንዲዘረጋ የሚመክር ነበር።

አምባሳደር ኮኸን ይህን ሐሳብ ያቀረቡት ኢትዮጵያ ያለ ባሕር በር መቅረቷ ወደፊት ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስና ለቀጣናዊ አለመረጋጋት እንደሚዳርጋት አስቀድመው በመረዳታቸው ቢሆንም የወቅቱ የኢሕአዴግ መሪዎች ግን ይህንን የረዥም ጊዜ ብሔራዊ ጥቅም ቸል በማለት ሐሳቡን ሳይቀበሉት ቀርተዋል።

ይህ የኸርማን ኮኸን ምክረ-ሐሳብ ተቀባይነት እንዳያገኝ የአሕአዴግ መሪዎች ሲቃወሙ እንደነበር መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የባሕር በር ጉዳይ ሲነሳም "ወደብ ተራ የንግድ ሸቀጥ እንጂ የሉዓላዊነት ጥያቄ አይደለም" በማለት ሲያጣጥሉት ነበር። አምባሳደር ኮኸን .. 2000 ባደረጉት ቃለ መጠይቅ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗ ስለሚያስጨንቃት አሰብን ልትመልስ ትችላለች ብለው ለተናገሩት ንግግር አመራሮቹ በወቅቱ በሰጡት ምላሽ ኤርትራውያን ከፈለጉ አሰብን "ለግመሎቻቸው መጠጫ" ሊያደርጉት ይችላሉ በማለት የሀገራችንን ታሪካዊና ሕጋዊ መብት አሳንሰው መመልከታቸው በታሪክ የሚታወስ ስህተት ሆኖ ተመዝግቧል።

የወቅቱ የሽግግር መንግሥት መሪዎች ይህን መሰል የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ የመስጠት ውሳኔ እንዲያሳልፉ ያስገደዳቸው አንዱ ምክንያት ከኤርትራ ሰዎች ጋር የነበራቸውን የትግል አጋርነት ላለማበላሸት ነበር። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በሀገር ውስጥ የነበሩ ተቃዋሚ ኃይሎችን ለማዳከም የነበረው ፍላጎት እንደሆነ ይነገራል።

የኢሕዘዴግ ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ በወቅቱ ለድርጅታቸው አመራሮች "አሰብን ለመያዝ ከሞከርን አሜሪካና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኢራቅ ኩዌትን በወረረች ጊዜ እንደወሰዱባት እርምጃ ዓይነት ማዕቀብና ጥቃት ይሰነዝሩብናል" የሚል የተሳሳተ ስጋት በማጋባት የባሕር በር ጥያቄው እንዲቀበር አድርገዋል የሚል ወቀሳ ይቀርብባቸዋል። ይህ "የኢራቅ-ኩዌት" ንጽጽር ግን አሰብ ለዘመናት የኢትዮጵያ አካልና አስተዳደር የነበረች መሆኗን ከግምት ውስጥ ያላስገባና መብቷን አሳልፎ ለመስጠት የቀረበ ሰበብ እንደነበር የዘርፉ ምሁራን ይተቻሉ።

በወቅቱ የነበረው የሽግግር መንግሥት የኢትዮጵያን የባሕር በር መብት አሳልፎ የሰጠበት መንገድ በሕግ ረገድም ከፍተኛ ጉድለት የነበረበት እንደሆነ ይገለጻል። የሽግግር መንግሥቱ በጊዜያዊነት የተቋቋመና የሀገርን ቋሚ ድንበርና የሉዓላዊነት መብት አሳልፎ የመስጠት የሕዝብ ውክልናም ሆነ የሕግ ሥልጣን ያልነበረው አካል ቢሆንም የኢትዮጵያን የወደፊት ትውልድ ለከፋ ችግር የሚዳርግ ውሳኔ አሳልፏል። ይህ ውሳኔ ኢትዮጵያን 90 በመቶ በላይ ለሚሆነው የውጭ ንግዷ በአንድ ወደብ ላይ ብቻ ጥገኛ እንድትሆን ያደረጋት ሲሆን፣ ለከፍተኛ የወደብ ኪራይ ክፍያና ለኢኮኖሚ መዳከም ምክንያት ሆኗል። አምባሳደር ኸርማን ኮኸን በቅርብ ጊዜያት በሰጧቸው ቃለ መጠይቆች በወቅቱ የቀረበው የጋራ ተጠቃሚነት ሐሳብ ባለመተግበሩ እና የወቅቱ መሪዎች በፈጸሙት ስህተት የተሰማቸውን ቅሬታ በተደጋጋሚ ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የጀመረችው የባሕር በር የማግኘት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ባለፉት ሦስት አሥርተ ዓመታት የተፈጸመውን ታሪካዊና ሕጋዊ በደል ለማረም የሚደረግ የህልውና ትግል ነው። አምባሳደር ኸርማን ኮኸን በወቅቱ ያቀረቡትና በወቅቱ መሪዎቹ ውድቅ ያደረጉት የጋራ የኢኮኖሚ ኅብረት ሐሳብ ዛሬም ለቀጣናዊ ትስስርና ለዘላቂ ሰላም እንደ አንድ መፍትሔ ሊታይ የሚችል መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ያስገነዝባሉ። የኢትዮጵያን የጋራ ተጠቃሚነት እና ቀጣናዊ ትስስር ፍላጎት ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ስለ ባሕር በር ጉዳይ ባነሱባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ያረጋገጡት ነው።

ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት መሆኗ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በሙሉ ለኢኮኖሚ ውህደትና ለጋራ ብልፅግና ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ጉዳዩ በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እልባት እንዲያገኝ መሥራት የትውልዱ ግዴታ ሆኗል።

በለሚ ታደሰ