Search

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ሓሙስ መጋቢት 10, 2018 131

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለ1447ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንኳን አደረሳችሁ ሙሉ መልዕክት እንደሚከተለው ቀርቧል፦

በሕዝበ ሙስሊሙ ዘንድ ዒድ አል ፈጥር የበረከት በዓል ተደርጎ ይታመናል። ረመዳንም የአላህ (ሱ.ወ) ደግነት የሚገለጥበት፣ ውድ ስጦታዎችን ለሰው ልጆች የሰጠበት ወር ነው። ቁርአን ወደ ምድር የወረደበት፣ ጅሃንም ተዘግቶ የጀነት በሮች የሚከፈቱበት፣ ሁሉም እንደ እምነቱ ጽናትና እንደ አላህ (ሱ.ወ) አዝዥነት ምንዳዎችን የሚያገኝበት ወቅት በመሆኑ ሕዝበ ሙስሊሙ ዘወትር የረመዳንና የዒድ አል ፈጥርን መምጣት በጉጉት ይጠብቃል።

በዒድ አል ፈጥር ከፈጣሪ በረከት የሚቸሩባቸው የረመዳንን ወር በጾምና በጸሎት ያሳለፉ ናቸው። በበዓሉ መምጣት የሚደሰቱትም ረመዳንን በመልካም ተግባር ለማሳለፍ የበረቱ ናቸው። በተቀደሰው ወር ከክፋት የተቆጠቡ፣ ለድሆችና አቅመ ደካሞች ዘካትን የሰጡ፣ የበደሏቸውን ይቅር ለማለት የደፈሩ በሐሴትና በመንፈሳዊ ኃይል ተሞልተው ለዒድ ይደርሳሉ። በተቃራኒው በጸሎት ያልነቃና ለመስጠት የሰሰተ ከፈጣሪ በረከት አያገኝም።

ከፊታችን ግንቦት ላይ የሚካሄደው ምርጫ ሀገራችን የዲሞክራሲ ድል የምትቀዳጅበት፣ ወደ ቀጣይ ብሩህ ዘመን የምትሻገርበት በር ነው። እንደ ሀገር ለዓመታት ዲሞክራሲን ስንናፍቅ ኖረናል። ጉዟችን አልጋ በአልጋ አልነበረም። ነገር ግን ከፈተና በሁዋላ በረከት፣ ከብርታት በኋላ ሐሴት እንዳለ ከረመዳን ጾምና ከዒድ አል ፈጥር በዓል እንማራለን።

መልካም የዘራ መልካም ምርት እንደሚያጭድ ሁሉ፣ አሽክላ የዘራውም አሜኬላ ያጭዳል። ስለተመኘን ብቻ አሜኬላው በመልካም ስብል አይለወጥም። በመንፈሳዊውም ሆነ በዓለማዊ ጉዳዮች ውስጥ የሥራ ውጤቶች ናቸው። ስለዲሞክራሲም ስናስብ ይህንን ሐቅ መዘንጋት የለብንም። የምንገነባው ሕጋዊና ሕዝባዊ መንግሥት የሚወሰነው በቅድመ ምርጫ ተሳትፎአችን ልክ ነው። ተሳትፎአችን ከጠነከረ ዲሞክራሲያችንም ይበልጣል። ደካማ ተሳትፎ አድርገን ጠንካራ ዲሞክራሲ ለማሳደግ መመኘታችን ሞኝነት ነው። ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በባዶ መሬት አይበቅልም፤ በጭቅጭቅና ሥርዓት አልበኝነትም አይገነባም። ይልቁንም ስኬትን ለትብብርና ቅንጅት ልብን ክፍት ማድረግን፣ በጨዋታው ሕግ መመራትን ይጠይቃል።

ረመዳን ቤተሰብ የሚገናኝበት፣ ጎረቤት የሚሰባሰብበት፣ ሰውነት የሚገነባበት እና መንፈስ የሚቀረጽበት ወር ነው። ዒድ አል ፈጥር ደግሞ የሰው ልጅ ጤናማ ግንኙነቶች የሚያመለክት በዓል ነው። የሰው ልጅ ከፈጣሪው ጋር፣ ከራሱ ጋር እና ከወገኑ ጋር የሚኖረው ግንኙነት ጤናማ ካልሆነ ጠቅላላ ሕይወቱ ጤናማ አይሆንም። በረመዳን ወቅት ጾሙ ሰዎችን ከራሳቸው ጋር ያገናኛቸዋል፤ ሰላትና ዱአ ከፈጣሪው ጋር ያገናኛቸዋል፤ ዘካና ሰደቃ ደግሞ ከማህበረሰቡ ጋር ያገናኛቸዋል። ኢትዮጵያውያን ጤናማ ሕይወትን መምራት እንድንችል እነዚህን ሦስቱን ጤናማ ማድረግ አለብን።

ሰው ከፈጣሪው እና ከራሱ ጋር ያለው ግንኙነት ጤናማ ካልሆነ ለማህበረሰቡም ለሀገርም ጠንቅ ነው። ሰው ከራሱ ጋር እየተጋጨ ከኖረ ከሁሉም ጋር ይጋጫል። ዛሬ ጦርነትን ባህል፣ ዝርፊያን ልምድ፣ ጥፋትን ዕለት-ተዕለት ድርጊት አድርገው የሚኖሩት ሰዎች የመጀመሪያው ትግራቸው ከፈጣሪያቸውና ከራሳቸው ጋር አለመስማማት ነው። በውስጣዊ ባሕርያቱ ያልተስማማ ሰው ከማንም ጋር አይስማማም። ዕርቅ፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ መግባባት እና መስማማት የሚባሉ ነገሮች አይገቡትም።

ሰው ከፈጣሪውና ከራሱ ጋር ከተስማማ ከማንም ጋር መስማማት ይችላል። ከአንገት በላይ ሳይቀር። "ለድንገት እንኳ ቢሆን የራራ ሰው በፍርድ ቀን (ቂያማህ) አላህ ይራራለታል።" ሲሉ ነብዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) ያስተማሩት ለዚህ ነው።

የእስልምና ዋናው መሠረቱ ሰላም የሆነው ለዚህ ነው። ሰላም ማለት ከራስና ከአካባቢ ጋር በጤናማ ግንኙነት ለመኖር መቻል ነውና።

የዘንድሮውን የዒድ በዓል ስናከብር በዓለማችን ስለ ሰላም የሚነገረውን ያህል የዓለም ሕዝቦች በሰላም መኖር ለምን አልቻሉም ብለን እንጠይቅ? የግጭትና የጦርነት ድንጋይ እየደጋገመ ለምን ይወረወራል? ከልማት ይልቅ ጥፋትን እንደ ጀብድ የሚያየው ልምምዳችን ለምን ገናና ሆነ? የሰው ልጅ ከጭቅጭቅና ከጦርነት የተረፈው ድህነትና ኋላ ቀርነት መሆኑን እያየን ለምን አልተማርንም? አልጠፋ ብለን በምንሠራው ዓለም የሚኖሩ ወገኖቻችን እንዴት ግጭትንና ጦርነትን የሚያበረታቱ ሆኑ? ይህ ትውልድ እነዚህን ጥያቄዎች በሚገባ አጢኖ ምላሽ ሊያገኝላቸው ይገባል።

ከራሳቸው ጋር ሰላም ያጡ አካላት የማኅበረሰቡን ሰላም እንዲረብሹ ልንፈቅድላቸው አይገባም። ከረመዳን ዕሴቶች ጋር የተጣሉ ሰዎች ዘመናችንን እንዲረብሹ ልንፈቅድላቸው አይገባም። በዐሥራ ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደ ሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን መኖር ቀድሞ መገኘት ነው። በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን እንደ ዐሥራ ሁለተኛው ክፍለ ዘመን መኖር ግን መረገም ነው። መግደል፣ ማገት፣ የገበሬውን እርሻ ማቃጠል፣ ሴቶችን መድፈር፣ ማኅበራዊ ተቋማትን መመዝበር፣ ቅርስና ታሪክን ማበላሸት፣ ጠብመንጃን የሁሉም ነገር መድኃኒት አድርጎ መውሰድ፤ እነዚህ ሁሉ ከ800 ዓመታት በፊት ያለፉ የሰው ልጅ ጠባዮች ናቸው።

ከሦስት አካላት ጋር የታረቁ ሰዎች ብርቱዎች ናቸው ይባላል፦ ከራሳቸው፣ ከማኅበረሰባቸው እና ከፈጣሪያቸው ጋር። እንደ ኢትዮጵያዊ እኛም ራሳችንን የገዛን፣ ፈጣሪን የምንፈራ እና ለማኅበረሰቡ ሰላምና ዕድገት የምንጨነቅ መሆን አለብን። ኢትዮጵያ የምታድገውና የምትበለጽገው በሁላችን እንጂ በሌላ አይደለም። ዜጎች ሲገነቡ ትገነባለች፤ ዜጎች ሰላም ሲሆኑ ሰላም ትሆናለች፤ ዜጎች ሲሰማሙ የብልጽግና ጉዞዋ ይፋጠናል:: የኢትዮጵያም መበልጸግ የሌላ ሳይሆን የእኛ መበልጸግ ነው። ስለሆነም ኢትዮጵያ እንድትበለጽግ የሚፈለግብንን መሥዋዕትነት ሁሉ የመክፈል ኃላፊነት የእኛ ነው። የእኛ ልፋት ከዛሬ አልፎ ለትውልድ ይተርፋል። ሀገር መውደዳችን የሚታወቀው እና መልካም ዜግነታችን የሚገለጠው በሥራችን ነው። ነቢዩ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) "ምርጥ ሰዎች ማለት ሌሎችን ለመጥቀም የበረቱ ናቸው" ብለው ያስተማሩት ለዚህ ነው። ይሄንን የዒድ አል ፈጥር በዓል እነዚህን መልካም ዕሴቶች እያሰብን፣ ሦስቱን ጤናማ መስመሮችም እያዳበርን እንድናከብረው አደራ እላለሁ።

በድጋሚ መልካም የዒድ አል ፈጥር በዓል ይሁን!

ዒድ ሙባረክ!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

መጋቢት ፣ 2018 ዓ.ም