ከ2012 ወዲህ ባሉ አምስት ዓመታት በተደረጉ ጠንካራ የተቀናጁ ኦፕሬሽኖች ከ53 ቢሊዮን ብር በላይ ኮንትሮባንድ በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ጠቅላይ አዛዥ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።
በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ እና በፀረ-ሙስ እና ኮሚሽን መካከል በተፈረመው የመግባቢያ ሰነድ መሠረት የሙስና ወንጀሎችን በመከላከል እና በመመርመር ሙሰኞችን ለፍትሕ በማቅረብ ረገድ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ከፌዴራል የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ጋር በዛሬው ዕለት በዋና መሥሪያ ቤት ተገምግሟል።
ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ በዚሁው ወቅት እንደገለጹት፣ ከፍተኛ ክፍተት ይታይበት የነበረውን የሙስና ወንጀሎችን የመከላከል እና የመቆጣጠር ተግባር ለማስተካከል በሪፎርሙ ትኩረት ተሰጥቶ በመሠራቱ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ከፍተኛ ውጤት ተመዝግቧል።
በተለይም ከፌዴራል የፀረ-ሙስና ኮሚሽን እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በተወሰደ እርምጃ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ 384 ሰዎች ተይዘው ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የሙስና እና የኮንትሮባንድ ወንጀሎች ትሥሥር እንዳላቸው የገለጹት ኮሚሽነር ጄኔራሉ፣ ከ2012 ወዲህ ባሉ አምስት ዓመታት ከ53 ቢሊዮን ብር በላይ ኮንትሮባንድ በቁጥጥር ሥር ማዋል መቻሉንና ይህም ከሪፎርሙ በፊት በነበሩ ዓመታት ከተመዘገበው ሁለት ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ጄኔራሉ አያይዘውም በዚህ ስድስት ወር ውስጥ ከሌሎች የፀጥታ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በተሠሩ የኦፕሬሽን ሥራዎች ከ14 ቢሊዮን ብር በላይ የወጪ እና ገቢ ኮንትሮባንድ በቁጥጥር ሥር መዋሉንም ገልጸዋል።
ሁለቱ ተቋማት ባለፈው ዓመት በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የጋራ የስምምነት ሰነድ ተፈራርመው ወደ ሥራ በመግባታቸው እንደ ሀገር በፀረ-ሙስና ትግል ላይ እየታየ ያለው ለውጥ እንደ ምሳሌ የሚጠቀስ እና ለሌሎች ሀገራትም ሞዴል መሆኑን ጠቁመዋል።
ጥቂት የዓለም ሀገራት የታጠቋቸውን ዘመናዊ የምርመራ መሣሪያዎችን በመጠቀም የምርመራ ሥራችን ግልጸኝነት የሰፈነበት እና ዓለም አቀፍ ስታንዳርዱን የጠበቀ እንዲሆን እየተሠራ ነውም ብለዋል።
ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ሙስናን ለመከላከል እየተደረገ ያለው ርብርብ ያለ ኅብረተሰቡ ትብብር ውጤታማ እንደማይሆን ጠቅሰው፤ ኅብረተሰቡ በሰው አልባ የፖሊስ አገልግሎት (Smart Police Station)፣ በEFP App መተግበሪያ እና በ991 ነጻ የስልክ ጥሪ ጥቆማ በመስጠት በተመዘገበው ስኬት ላይ የነበረው ድርሻ ከፍተኛ እንደነበር ተናግረዋል።
የፌዴራል የሥነ-ምግባር እና የፀረ-ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ሳሙኤል ኡርቃቶ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከል እና የምርመራ ሥራን ዘመናዊ እና ተወዳዳሪ ለማድረግ እያከናወነ ያለው ተግባር እንደ ሀገር የሚያኮራ ነው ብለዋል።
እየተፈጠረ ያለው ከፍተኛ አቅም የሙስና ወንጀሎችን በመከላከል እና ተግዳሮት የነበሩ የዘልማድ አሠራሮችን በዲጂታል በመተካት ለፀረ-ሙስና ትግል ውጤታማነት የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኮሚሽነሩ ሁለቱ ተቋማት እንደ ሀገር እየተካሄደ ባለው የፀረ-ሙስና ትግል ላይ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው አንስተው፣ በጥምረት ባከናወኑት ሥራ ስኬት በማስመዝገብ ሀገራችን ሙስናን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በምትወስደው ጠንካራ እርምጃ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትመሰገንና በመልካም ስም የምትነሳ ሆናለች ማለታቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
#Ethiopia #FederalPolice #AntiCorruption