Search

ነዳጅን በቁጠባ በመጠቀም የኢኮኖሚ ጫናውን እንቀንስ፡- ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር

ረቡዕ መጋቢት 09, 2018 52

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን የነዳጅ አቅርቦት እጥረት ተከትሎ፣ ዜጎች ያለውን ነዳጅ በኃላፊነት ስሜትና በቁጠባ እንዲጠቀሙ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።
ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ በመካከለኛው ምስራቅ የተፈጠረው ግጭት በዓለም አቀፍ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል በመፍጠሩ፣ የመጣውን የነዳጅ እጥረት ለመቋቋም አላስፈላጊ የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎችን በመገደብ ነዳጅን መቆጠብ ይገባል።
መንግሥት በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የኑሮ ውድነት ጫና ለመቀነስ በነዳጅ ግዢ ላይ ከፍተኛ ድጎማ እያደረገ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ዓለሙ፤ ይህም በተለይ በትራንስፖርትና በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይ የሚፈጠርን ድንገተኛ የዋጋ ጭማሪ ለመግታት ትልቅ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ ያለውን ውስን ሀብት በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ዜጎች ነዳጅን ለአስፈላጊ ጉዳዮች ብቻ እንዲጠቀሙና የቁጠባ አማራጮችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።
በዚህም አጫጭር ጉዞዎችን በእግር በመጓዝ፣ ከተናጥል ተሽከርካሪ ይልቅ የብዙኃን ትራንስፖርት አማራጮችን በመጠቀም፣ በቤተሰብ ውስጥ ያሉ ተሽከርካሪዎችን ቁጥር በመቀነስ በጋራ በመጠቀም እንዲሁም እንደ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ያሉ አማራጮችን በስፋት እንዲተገብሩ አሳስበዋል።
እነዚህን የቁጠባ እርምጃዎች መተግበር በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ለሀገር ማሰብና የኢኮኖሚ ጫናውን ለመቋቋም አቅም የሚሰጥ ተግባር መሆኑንም ሚኒስትሩ አክለው ገልጸዋል።
በዓለም ይልፉ