ደቡብ ኮሪያ የከፋውን የጨለማ ዘመን የተሻገረችው አንድ ሆና ነው፤ መከፋፈል ለሀገር ውድቀት ይዳርጋል ይላሉ የዓለም አቀፍ ወጣቶች ኅብረት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር የሆኑት ናም ፕል ህዩን (ዶ/ር)፡፡
በየትኛውም ሀገር መከፋፈል፣ ፈተና እና ውድቀት መኖሩን የሚገልጹት ዶ/ር ናም፤ ደቡብ ኮሪያውያን በሀገራዊ አጀንዳ ላይ አንድ ሆነው በጋራ በመቆማቸው የጨለማውን ዘመን ተሻግረው ዛሬ ላይ ምሳሌ መሆን ችለዋል ነው ያሉት።
ከደቡብ ኮሪያ በተጨማሪ እንደ ቻይና ያሉ ሌሎች ሀገራትም ከውድቀታቸው ተነስተው ከፍታ ላይ የመድረሳቸው ምስጢር በአንድነት መቆማቸው ነው ብለዋል፡፡
ደቡብ ኮሪያ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ብሔራዊ ኪሳራ በገጠማት ወቅት፣ ዜጎቿ ያላቸውን ጥሪት ለሀገራቸው በመስጠት ሀገሪቱ ከነበረችበት ዕዳ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንድትወጣ ማስቻላቸውን አውስተዋል፡፡
በዚህ የሚያስደንቅ የሕዝብ ቁርጠኝንነት እና አንድነት፣ ሀገሪቱ ከነበረችበት ጉስቁልና አሁን ወዳለችበት ክብር እና ልዕልና ተሸጋግራለች ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያም አሁን እየሄደችበት ያለው የቁጭት የዕድገት ጎዳና መነሳሳትን የፈጠረ ስለመሆኑ ነው ዶ/ር ናም የሚገልጹት።
በኢትዮጵያ አሁን ያለው ትውልድም የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በመውሰድ፣ በተሰማራበት ዘርፍ የሚሰጠውን ኃላፊነት ተግቶ በመወጣት ሀገሪቱ ወደ ቀደመው ልዕልናዋ እንድትመለስ መሥራት ይገባዋል ነው ያሉት።
በሄለን ተስፋዬ