Search

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ80 ዓመታት ጉዞ

ዓርብ ጥቅምት 14, 2018 50

ዛሬ ጥቅምት 24 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቀን ነው፤ ድርጅቱ ልክ የዛሬ 80 ዓመት እ.አ.አ ጥቅምት 24 ቀን 1945 ተመሠረተ።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃትን ተከትሎ የተቋቋመውን ይህን ድርጅት ከመሠረቱት እና በመመሥረቻ ቻርተሩ ላይ በቀዳሚነት ፊርማቸውን ካኖሩ 50 ሀገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት።

ሌላ ተመሳሳይ የዓለም ጦርነት እንዳይከሰት ለመከላከል፣ በዓለም ዙሪያ ሰብአዊ መብቶች ለማስከበር፣ እንዲሁም ለመላው የዓለም ሕዝብ ዘርፈ ብዙ ጠቃሚ ጉዳዮችን መከወንን ዓላማው አድርጎ የተመሠረተው ይህ ድርጅት የ80 ዓመት ጉዞው ሲታወስ፣ በተቋቋመበት ቻርተር መሠረት ማሳካት የቻላቸው ነገሮች የመኖራቸውን ያህል ማድረግ ሲገባው ያልቻላቸው እና እንደ ድክመት የሚጠቀሱ ነገሮችም ይነሣሉ።

ይህ ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ ዋና ዋና ዓላማዎችን በማሳካት ረገድ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

ከነዚህም መካከል የድርጅቱ ዋነኛ ስኬቱ ተብሎ የሚጠቀሰው ሌላ አውዳሚ  የዓለም ጦርነት እንዳይከሰት መከላከል መቻሉ እና በታላላቅ ሀገራት መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በውይይት እንዲፈቱ የውይይት መድረክ ሆኖ ማቀራረቡ ነው።

በሌላም በኩል ተመድ በሰብአዊ ዕርዳታ፣ በአካባቢ ጥበቃ እና ጤና አጠባበቅ ላይ የራሱን ጉልህ ሚና ማሳካት ችሏል።

ከነዚህም መካከል በዋነኛነት የሚጠቀሰው የዓለም ጤና ድርጅትን በመጠቀም እንደ ፈንጣጣ ያሉ ለሚሊዮኖች ሞት እና አካል ጉዳት ምክንያት የነበሩ በሽታዎችን መከላከል እና ማጥፋት መቻሉ ነው።

በተጨማሪም በዓለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) አማካኝነት በተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የሰብአዊ ዕርዳታን ለሚፈልጉ በመቶ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች መድረስ በመቻሉ ይመሰገናል።

በሌላም በኩል በዘመነ አፓርታይድ በተለይም በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ነፃነታቸውን እንዲያገኙ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን ሠርቷል። በዚህም ብዙ ሀገራት ነፃነታቸውን አግኝተው ራሳቸውን ማስተዳደር ችለዋል።

የሰላም አስከባሪ ኃይሉን በመጠቀም በናሚቢያ፣ ሴራሊዮን፣ አንጎላ፣ ሞዛምቢክ፣ ላይቤሪያ እና ብሩንዲ፣ ካምቦዲያ፣ ኤልሳልቫዶር፣ ጓቲማላ፣ ምሥራቅ ቲሞር እና በሌሎች ሀገራት የርስ በርስ ግጭቶችን በማስቆም የብዙዎችን ሕይወት ማዳን ችሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በ80 ዓመት ዕድሜው እጅግ ብዙ መልካም ተግባራትን ያከናወነ ድርጅት መሆኑ የማይካድ ቢሆንም በሌላ በኩል ማድረግ ሲገባው ወይም ሲችል፣ ሳያደርግ በመቅረቱ፣ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት መወጣት አልቻለም የሚሉ ትችቶችም ጥናት ባካሄዱ የፖለቲካ ተንታኞች ይቀርቡበታል።

ከነዚህም መካከል በ1994 በሩዋንዳ የተፈፀመው አሳዛኝ የዘር ማጥፋት እና በ1995 በቦስኒያ የተፈፀመውን ተመሳሳይ እልቂት ያነሣሉ።

ተመድ እነዚህ እልቂቶች ከመከሰታቸው በፊት የሁኔታውን አሳሳቢነት በመረዳት በቂ ወታደራዊ ኃይል ባለማሰማራቱ ይወቀሳል።

እንዲሁም ኃያላን ሀገራት በተለያዩ ምክንያቶች በሌሎች ሀገራት ላይ ያደረጉትን ወረራ እና የሀገራትን የእርስ በርስ ጦርነት እና ውድመት ለማስቆም አቅም ያንሰዋል የሚለው ሌላው ትልቁ የሚወቀስበት ጉዳይ ነው።

ከነዚህም መካከል በኢራቅ፣ ሊቢያ፣ የመን፣ አፍጋኒስታን፣ ፍልስጤም እና በሌሎች ሀገራት በኃያላን መንግሥታት በተደረገ ጥቃት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰወች ለሞት እና ለአካል ጉዳተኝነት ተዳርገዋል።

ሀገራቱ ፈራርሰው ለእርስ በርስ ግጭት ተዳርገዋል፤ ይህም ለሚሊዮኖች ስደት እና ሞት ምክንያት ሆኗል።

የተባበሩት መንግሥታት እነዚህን የተከሰቱትን የእርስ በርስ ጦርነቶች እና የውጭ ጣልቃ ገብነቶች ማስቆም አልቻለም። ይህም የዓለም አቀፍ ሕግ የበላይነት እንዲሸረሽር አስተዋጽኦ አድርጓል የሚሉት ጉዳዮች እንደ ድክመት የሚቆጠሩበት ነገሮች ናቸው።

የፖለቲካ ተንታኞቹ አያይዘውም ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ተመድ የያዘውን ሥልጣን በአግባቡ ለመጠቀም አስቸኳይ ለውጦችን ማድረግ እንደሚኖርበት ይገልጻሉ።

ከነዚህም መካከል የፀጥታው ምክር ቤት የአፍሪካ፣ የእስያ እና የላቲን አሜሪካ ሀገራትን በቋሚነት እንዲወክሉ በማድረግ የውክልና ክፍተቱን መሙላት አንዱ እንደሆነ ያነሣሉ።

ብዙ ውሳኔዎች ላይ መሰናክል እየሆነ ያለውን የቬቶ ፓወር (ድምፅን በድምፅ የመሻር ሥልጣን) አጠቃቀምን በተለይም በጅምላ ጭፍጨፋ ወንጀሎች ላይ መገደብ ሌላኛው ሐሳብ ነው።

ግጭትን ቀድሞ የመከላከል አቅም ማዳበር፣ ከግጭት በኋላ ዕርዳታ ከመስጠት ይልቅ ጦርነት ሳይጀመር በዲፕሎማሲ እና በመረጃ በመታገዝ ቀድሞ የመከላከል አቅምን ማጠናከርም ይጠቀሳል።

የተልዕኮዎች ጥራትን በተመለከተ ደግሞ የሰላም አስከባሪ ኃይሎችን ማጠናከር፣ እንዲሁም ሥነ ምግባራዊ ብቃታቸውን በማረጋገጥ ወሳኝ እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን በመስጠት ውጤታማነታቸውን ማሳደግ እና ድርጅቱን በሁሉም መልኩ ማሳደግ የሚያስችሉ ሥር ነቀል ለውጦችን ማድረግ ይኖርበታል የሚል ነው።

በዋሲሁን ተስፋዬ

#EBC #ebcdotstream #UN #UNDay