Search

አረንጓዴ ዐሻራ ሕዝብ ለዓላማ ከተንቀሳቀሰ ተዓምር መሥራት እንደሚቻል ምስክር ነው - ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ

ዓርብ ጥቅምት 14, 2018 30

የአረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ አንድ ሀገር ለጋራ እና ዘላቂ ዓላማ ሲንቀሳቀስ ተዓምር መሥራት እንደሚችል ትምህርት የሚወሰድበት እንደሆነ ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ ገለጹ።

ፕሬዚዳንቱ መቀመጫውን ብራሰልስ ካደረገው ‘ዲፒሎማቲክ ማጋዚን’ ከተሰኘ የኦንላይን መጽሔት ጋር ባደረጉት ቆይታ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ደኅንነት ከአካባቢዋ ጤና ጋር የተቆራኘ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በስብጥር ሥነ-ሕይወት የታደለች መሆኗን እና ከ16 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚታረስ መሬት የሚታረስ መሬት እንዳላት ገልጸው፣ ይሁን እንጂ ልክ እንደ ሌሎቹ የቀጣናው ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በሚፈጠሩ ተግዳሮቶች ግንባር ተጠቂ እንደሆነች አንሥተዋል። 

የተራዘመ ድርቅ እና የተዛባ ዝናብ ባስከተሏቸው ተፅዕኖዎች የሰብል ምርት እና የሰዎች የምግብ ዋስትና ላይ አደጋ ጋርጦ መቀጠሉን ያወሱት ፕሬዚዳንቱ፣ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ዐሻራ ኢኒሼቲቭ ለዚህ ፈተና ምላሽ የሚሰጥ ወሳኝ እና ንቁ ምላሽ መሆኑን ገልጸዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ የተፈጥሮ ቅርሶቻችንን ለመጠበቅ፣ የደን ልማትን ለማፋጠን እና አስፈላጊ የሆኑ ሥነ-ምኅዳሮችን ወደነበረበት ለመመለስ ያለው አጠቃላይ ሀገራዊ ቁርጠኝነት ማሳያ እንደሆነም አውስተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት በተጀመረው ኢኒሼቲቩ፣ ባለፉት ሰባት ዓመታት በመላ ሀገሪቱ ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በተሳካ ሁኔታ መትከል ተችሏል ብለዋል።

ይህ ሀገራዊ ጥረት የኢትዮጵያን የደን ሽፋን በ1990ዎቹ ከነበረበት 3.4 በመቶ ወደ 23.6 በመቶ ማሳደጉን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ የውኃ ምንጮችን በመመለስ፣ የአፈር ክለትን በማስቀረት፣ የአፈር ለምነትን በማሻሻል እና የካርቦን ልቀትን በመቀነስ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን አብራርተዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ ዛፎችን መትከል ብቻ ሳይሆን ወሳኝ እና ዘላቂ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና የሰው ልጆች ኑሮን ማሻሻያ እንደሆነም አውስተዋል።

እንደ ቡና፣ አቮካዶ እና ፓፓያ ያሉ ፍሬ የሚያፈሩ እና ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውን ዝርያዎች ስልታዊ በሆነ መንገድ በማካተት የሀገር ውስጥ የምግብ ሥርዓቶችን በቀጥታ በማጠናከር፣ የአመጋገብ ሥርዓትን በማጎልበት እና ኢኮኖሚያዊ ዕድሎችን እየፈጠረ እንደሆነም ጠቅሰዋል።

ይህ የአካባቢ ተሃድሶ እና የግብርና ምርታማነትን በማሻሻል የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ግባችን ማዕከላዊ ሲሆን፣ እንደ የበጋ ስንዴ ምርት ኢኒሼቲቭ ካሉ ሌሎች ብሔራዊ ፕሮግራሞች ጋር የተቆራኘ ነው ብለዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ ከሀገራዊ ተፅዕኖው ባሻገር ዓለም አቀፋዊ አጀንዳ እየቀረፀ መሆኑን እና ሀገር በቀል መፍትሔዎችን ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖ ሊኖራቸው እንደሚችል እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።

በአንድ ወቅት በዋነኛነት የአየር ንብረት ቀውስ ሰለባ ሆና ትታይ የነበረው ኢትዮጵያ አሁን አረንጓዴ እና ኢኮኖሚን በመገንባት የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ለአፍሪካ አርአያ የሚሆን ሥራ እየሠራች መሆኑን ያሳየ መሆኑን ጠቅሰዋል ፕሬዚዳንት ታየ።

በለሚ ታደሰ

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #GreenLegacy