የባሕር በር ጥያቄ ጉዳይ ከዚህ በኋላ ወደ ኋላ መመለስ የማይችልበትና አሁን ላይ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚቆጭበት አጀንዳ ሁኗል ሲሉ የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ስሁል ገለጹ።
አቶ ነብዩ ከኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳንኤል ኦላኔ ጋር በጋራ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም እና ጂኦስትራቴጂካዊ ቁመና” በሚል ሀሳብ በኤ.ፍ ኤም አዲስ 97.1 የቀጥታ ስርጭት ላይ ውይይት አድርገዋል።
አቶ ነብዩ፥ ኢትዮጵያ ወደብ የነበራት እና አሁንም የሚገባት ትልቅ አገር እንደሆነች ገልጸው፤ ይህ አጀንዳዋ እንዲሳካ መንግሥት ቁርጠኛ አቋም ይዞ እና ህብረተሰቡም ይህን አቋም ደግፎ እየታየ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የባሕር በር ጉዳይ እንደ ጥያቄ ለማንሳት ይፈራ የነበረ፤ እንደውም እንዲረሳ እና እንዲዳፈን ይፈለግ የነበረ መሆኑን አንስተዋል።
አሁን ላይ ግን የባሕር በር ጉዳይ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ የሚቆጭበት ሁኗል ሲሉ ገልጸው፤ ይህ የብሔራዊ ጥቅም አጀንዳ ከሶስት ነገሮች ማለትም ከህዝቡ፣ ከመንግሥት እና ከታሪክ የመነጨ መሆኑን አብራርተዋል።
ብሔራዊ ጥቅም ውጭ ሂደን የምንፈልገው ነገር ሳይሆን በዋነኝነት ውስጥ ያለ ጉዳይ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ አንድ ሁነን ውስጣችን ሲጠነከር፣ ኢኮኖሚያችን ሲያድግ ለትብብር የምንፈለግ ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል።
በአጠቃላይ እንደ ሀገር አሁን ለማሳካት እየጣርነው ያለው የብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ በፊት የነበረ እና በአንድ የታሪክ ስህተት ያጣነው ነው ብለዋል።
ይህ ብሔራዊ ጥቅማችን በድጋሚ መረጋገጡ ግን አይቀሬ ነው ብለው ይህን ለማሳካትም የእያንዳንዱ ህብረተሰብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አክለዋል።
#ebcdotstream #nationalintrrest #ብሔራዊጥቅም #seaport