የኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የ1 ሺህ 800 ሜጋ ዋት የታዳሽ ኃይል ምንጭ ብቻ ሳይሆን፣ የሀገሪቱን የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ ትልቅ አቅም የሚፈጥር ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ‘የሚኒስትሮች ምክር ቤት ምልከታ በኮይሻ’ የውይይት መድረክ ላይ እንዳሉት፥ ፕሮጀክቱ የለውጡ መንግሥት ከታደጋቸው ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ነው።
ፕሮጀክቱን ለ4ኛ ጊዜ መጎብኘታቸውን የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሥራው በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
የኮይሻ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ ትልቁ የኦሞ ወንዝ የሚፈስበት፣ በዙሪያው መዝናኛዎችን ለመገንባት ምቹ ከባቢ ያለው በመሆኑ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ ትልቅ አቅም የሚፈጠር ነው ብለዋል።
የዱር እንስሳት መገኛ የሆነው እና አረንጓዴ የለበሰውን የጨበራ ጩርጩራ ለምለም ምድር ቱሪስቶች ሲጎበኙት ማየታቸውን ገልጸው፤ ወደፊትም የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን ከኮይሻና ከሌሎች መስህቦች ጋር ማስተሳሰር እንደሚገባም አሳስበዋል።
በላሉ ኢታላ
#EBC #EBCdotstream #PMOEthiopia #projects #koysha