በሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስቀጠል ከቻልንባቸው ምክንያቶች አንዱ የዕይታ ለውጥ መደረጉ ነው ሲሉ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ እና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማ ከሚኒስትሮች ጋር በመሆን በኮይሻ ግድብ አካሂደዋል።
አቶ አደም ፋራህ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ ከ100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም እና የኢኮኖሚ ዕድገት አዝማሚያዎች ጋር በተያያዘ የተገኘው ስኬት የሦስት ቁልፍ ጉዳዮች ድምር ውጤት ነው።
በጂኦ ፖለቲካ ውጥረት፣ በኢ-ተገማች የታሪፍ ዲፕሎማሲ፣ በአቅርቦት ሰንሰለት መቆራረጥ ምክንያት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢኮኖሚ ዕድገት መቀዛቀዝ ብሎም የተዳከመ ማክሮ ኢኮኖሚ ዐውድ በሚታይበት ሁኔታ በሀገራችን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ማስቀጠል ችለናል ነው ያሉት።
ለዚህ አመርቂ ውጤት ያበቃን የሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ድምር ውጤት ነው ያሉት አቶ አደም፣ የመጀመሪያው ከለውጡ ወዲህ የዕይታ ለውጥ (ፓራዳይም ሺፍት) ማምጣት መቻል እንደሆነ ገልጸዋል።
ሌሎቹ ምክንያቶች ደግሞ የአመራሩ የማስፈጸም ዐቅም፣ ትጋት እና ቁርጠኝነት እንዲሁም የሕዝቡ፣ የግሉ ሴክተር፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፎ እና ትብብር ማደግ እንደሆኑ ጠቁመዋል።
መንግሥት ሕዝቡ በተደጋጋሚ ሲያነሣቸው የነበሩትን የኑሮ ውድነትን ማቃለል፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ቀልጣፋ እና ውጤታማ የማድረግ፣ ከሰላም እና ፀጥታ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ከሕዝብ ጋር በመሆን በሂደት እየተቃለሉ እንዲሄዱ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረጉን ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎም ተጨባጭ ለውጦች መመዝገባቸውን እና ቀሪ ሥራዎችንም በቀጣይ ከሕዝቡ እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን መንግሥት ለመፍታት ርብርቡን እንደሚያስቀጥል ገልጸዋል።
#EBC #ebcdostream #Ethiopia #economicgrowth #growth