Search

ለ15 ዓመታት የሚቆይ ብሔራዊ የአቮካዶ ልማት ፕሮግራም ይፋ ሆነ

ቅዳሜ ጥቅምት 15, 2018 64

‎በዛሬው ዕለት ለ15 ዓመታት የሚቆይ ብሔራዊ የአቮካዶ ፕሮግራም መጀመሩን የግብርና ሚኒስትሩ አዲሱ አረጋ ገለጹ፡፡
‎ብሔራዊ የልማት ፕሮግራሙ ወደ 38.57 ቢሊዮን ብር በጀት የተመደበለት መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ በቀጣይ ዓመታት የሚተገበር እንደሚሆነም ገልጸዋል።
‎‎ፕሮግራሙ የአቮካዶ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ዋነኛ ትኩረቱ ያደረገ እና አሁን ከተደረሰበት ከ100 ሺህ ሄክታር በአቮካዶ የለማ መሬት ወደ 191 ሺህ ሄክታር ማስፋፋትን ያለመ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
"አሁን የደረስንበት የምርታማነት መጠን ከ13 ቶን በሄክታር ወደ 24 ቶን በሄክታር በማሳደግ ዓመታዊ የምርት መጠናችንንም በዓመት ከ400 ሺህ ቶን ወደ 3.8 ሚሊየን ቶን ከፍ ለማድረግ ያለመ ነው" በማለት የብሔራዊ ፕሮግራሙን ግብ ጠቁመዋል።
 
‎ብሔራዊ የልማት ፕሮግራሙ የድህረ-ምርት ብክነትን መቀነስና ጥራትን ማስጠበቅ፣ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ግብይትን ማሻሻል፣ በአቮካዶ እሴት ሰንሰለት የምርምር፣ ሥልጠና እና ኤክስቴንሽን ሥርዓት አቅምን ማሳደግ ላይ በማተኮር እንደሚሠራም አቶ አዲሱ ገልጸዋል።
‎‎በዚህ ፕሮግራም 3 ሚሊዮን ባለአነስተኛ ይዞታ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ እና ፕሮግራሙ ሙሉ በሙሉ ሲተገበር ኢትዮጵያን ግንባር ቀደም የአቮካዶ ላኪ እንደሚያደርጋት ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
በክላስተር እየለማ በሚገኘው የአቮካዶ ምርት ከሀገር ውስጥ የምግብ ፍጆታ ባለፍ ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እየተገኘበት መሆኑ ተመላክቷል።
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሎሜ ወረዳ አቮካዶ እያመረቱ የሚገኙ አርሶ አደሮች በበኩላቸው፤ ምርቱ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እያስገኘላቸው መሆኑን ተናግረዋል።
 
በሂሩት እምቢአለ