የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ነብዩ ስሁል፤ አንድ ሀገር ሀገር የሚባለው ብሔራዊ ጥቅሙን አውቆ ለማስፈፀም ሲንቀሳቀስ በመሆኑ "ብሔራዊ ጥቅማችን ይሄ ነው" ብሎ መበየን እንደሚያስፈልግ ከኤፍኤም አዲስ 97.1 ጋር ባደረጉት ቆይታ ተናግረዋል።
ብያኔውንም በሶስት መንገድ መስጠት ይቻላል ያሉት አቶ ነብዩ፤ የመጀመሪያው በነባራዊ እውነታ ማለትም በግዛት ህልውና ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልፀዋል።
ሁለተኛው ከግዛት ባሻገር በእያንዳንዱን ዜጋ ደህንነት እና ባህላዊ ትውፊቶች ላይ የተመሰረተ የብሄራዊ ጥቅም ብያኔ መሆኑን ነው ያነሱት።
ሶስተኛው ደግሞ መሬት ላይ ተግባራዊ ሆኖ ዜጎች ይሄን አይነት ብሔራዊ ጥቅም አለን ብለው የሚተርኩት ነው ብለዋል አቶ ነብዩ ስሁል።
የእነዚህ ብያኔዎች ድምር ውጤትም አንዲትን ሀገር ሉዓላዊት፣ ደህንነቷ የተረጋገጠ፣ ከራሷ አልፋ ለሌሎች የምትተርፍ ኃያል ሀገር ያደርጋታል ሲሉ ገልፀዋል።
የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ ዳንኤል ኦላኔ በበኩላቸው፤ ብሔራዊ ጥቅምን ከሌሎች ጥቅሞች የበላይ የሚያደርገው የብዙኃኑ የተደመረ ጥቅም በመሆኑ ነው ብለዋል።
ብሔራዊ ጥቅም ህዝብን ካልጠቀመ ትርጉም የለሽ ይሆናል የሚሉት ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ የእያንዳንዱ ዜጋ የዕለተ ተዕለት እንቅስቃሴ ከአንዲት ሀገር ብሔራዊ ጥቅም ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሴራን ታደሰ
#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #national_interest