በኢትዮጵያ ሀሳቡን በትክክል መሬት ማውረድ፣ አካሄዱንም ከህዝብ ተጠቃሚነት ጋር ማቆራኘት የሚችል አስተዳደር መኖሩን ማየት ችያለሁ፤ በዚህም ሀገር ታሪኳን እየፃፈች እንደሆነ ተረድቻለሁ ሲሉ በሚኒስትር ማዕረግ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሀላፊ እናታለም መለሰ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማን ከሚኒስትሮች ጋር በመሆን በኮይሻ ግድብ አካሂደዋል።
በሚኒስትር ማዕረግ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሀላፊ እናታለም መለሰ በዚሁ ወቅት ባቀረቡት የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ፥ በመላው ዓለም መሪዎች በ100 ቀናቸው ምን ሠሩ በሚል የህዝብን ትኩረት የሚስቡ ዜናዎች ይሰራጫሉ ብለዋል።
አፍሪካ ግን ይህን ለመስማት ያልታደለች ናት ይላሉ፣ ተቺዎች ነው ያሉት፤ መነሻቸውም፣ አፍሪካውያን አያልሙም፣ ቢያልሙም አይተገብሩም የሚል ነው ሲሉ በቁጭት ገልጸዋል።
የአፍሪካ ኩራት በሆነችው ኢትዮጵያ ግን በተለይ ከለውጡ ወዲህ እንደ አንዲት ዕድለኛ ኢትዮጵያዊት የሚያልም፣ የሚተገብር እንዲሁም በ100 ቀናት ውስጥ የሚነገር ታሪክ የሚሠራ የመንግሥት አስተዳደር መኖሩን ለማየት ችያለሁ ነው ያሉት።
ዜጎች በእያንዳንዱ ዕለት ጓዳቸው የሚገባ ታሪክ መስማት ይፈልጋሉ ያሉት ሀላፊዋ፤ ተደማሪ የኢኮኖሚ ለውጡ እያስገኘው ያለውን ምርታማነት አርሶ አደሩ ከጓዳው አልፎ ወደ ገበያ ይዞት ከሚሄደው ምርት መገንዘባቸውን ተናግረዋል።
የ100 ቀናት ሪፖርቱ የፋብሪካዎች ምርት መጨመሩን እና መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግር መኖሩን ያስረዳ፤ ሀገር በእያንዳንዱ ቀን ምን ያህል እየተገነባች እንዳለች ያሳየ ነው ሲሉም ነው የገለጹት።
በሄለን ተስፋዬ
#ebcdotstream #ethiopia #koysha