በዓለም ዙሪያ ያለው ነባራዊ ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር በተሻለ ሁኔታ እያደገች ነው ሲሉ የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማን በኮይሻ ግድብ ከሚኒስትሮች ጋር አካሂደዋል።
ኢንጂነር አይሻ በዚሁ ወቅት፥ ዓይኖቻችንን ካስቀመጥናቸው ግቦች ሳንነቅል በመሥራት እያደረግነው ባለው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር አመርቂ ውጤት እየተገኘ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሀገራዊ የሆኑ አስተሳሰቦችን በማካተት በኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በማዕድን እና በሌሎችም ዘርፎች በራስ አቅም እየተከናወነ ባለው ሥራ የሚታይ ለውጥ መምጣቱን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ እና በሌሎች ከተሞች እንዲሁም በገጠር የተከናወኑ እና እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎችም የህዝቡን የአኗኗር ዘይቤ እና ሕይወት በመቀየር ረገድ ትልቅ ትልቅ ውጤት የተገኘባቸው መሆኑን አንስተዋል።
በእነዚህ ሥራዎች አፈፃፀም ሂደት የመፍጠር እና መፍጠን መርህን በመከተል የሥራ ባሕል አብዮት ማምጣት ስለመቻሉም ጠቅሰዋል።
አቅማችንን ለይተን አውቀን በቀጣናዊ ትስስር ላይ ጭምር በርትተን በመሥራታችን ተፅዕኖ ፈጣሪነታችንንም ማሳደግ ችለናል ነው ያሉት የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ።
በቢታንያ ሲሳይ