Search

ፒኬኬ ታጣቂዎቹን ከቱርኪዬ ማውጣት መጀመሩን አስታወቀ

እሑድ ጥቅምት 16, 2018 44

የኩርዲስታን ሠራተኞች ፓርቲ (ፒኬኬ) ታጣቂ ቡድን ታጣቂዎቹን ከቱርኪዬ ማውጣት መጀመሩን አስታውቋል።

የቀድሞው አማጺ ቡድን ከቱርኪዬ መውጣት የጀመረው ከነፍጥ ትግል ይልቅ ትጥቅ በመፍታት በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ለመሰማራት ከቱርኪዬ መንግሥት ጋር ከስምምነት ላይ መድረሱን ተከትሎ ነው።

ፒኬኬ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፥ ታጣቂዎቹን ትጥቅ የማስፈታት እና ከቱርኪዬ የማስወጣቱ ሂደት ከሀገሪቱ መንግሥት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረት በቅንጅት ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አስታውቋል።

እ.አ.አ ከ1984 ጀምሮ መንግሥትን በመቃወም ሰርጎ ገቦችን አደራጅቶ ወደ ትጥቅ ትግል የገባው የፒኬኬ ታጣቂ ቡድን ለ40 ሺህ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ፒኬኬ በመግለጫው፥ ለነፃ፣ ዴሞክራሲያዊ እና በወንድማማችነት ላይ ለተመሠረት ሕይወት ሲል ሁሉንም ታጣቂዎቹን ከቱርኪዬ ግዛት ለማስወጣት መወሰኑን ገልጾ፤ ቡድኑ ወደ ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ ለሚያደርገው ሽግግር የቱርኪዬ መንግሥት አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጥር ጠይቋል።

የሀገሪቱ ገዢ ፓርቲ ኤኬ ቃል አቃባይ ኡመር ቼሊክ በበኩላቸው፥ የታጣቂ ቡድኑ ከቱርኪዬ የመውጣት ውሳኔ የሀገሪቱ መንግሥት “ከሽብር የጸዳች ቱርኪዬ”ን ለመፍጠር ባስቀመጠው ግብ መሠረት የተገኘ ተጨባጭ ውጤት ነው፤ በቀጣይ አስፈላጊውን ሕጋዊ ማዕቀፍ ለማበጀትም በር ይከፍታል ብለዋል።

ታጣቂ ቡድኑ በእስር ላይ ባለው መሪው አብደላ ኦቻላን አማካኝነት ትጥቅ በመፍታት የሰላማዊ ትግል አማራጭን እንዲከተል የቀረበለትን ጥሪ በመቀበል በግንቦት ወር ከቱርኪዬ መንግሥት ጋር ከስምምነት ላይ ደርሶ እንደነበር የሮይተርስ ዘገባ አስታውሷል።

በመሐመድ ፊጣሞ

#ebcdotstream #turkiye #pkk #withdrawal