በሀገር ግንባታ ሒደት ጨረስን ብሎ መቆም እንደሌለ እና ለሀገር ልማት የሚውል ሥራ በመፈለግ ሁልጊዜም መትጋት እንደሚገባ የኮይሻ ፕሮጀክት ትምህርት ሆኗል ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያ 100 ቀናት የማክሮ ኢኮኖሚ አፈፃፀም ግምገማን በኮይሻ ግድብ ከሚኒስትሮች ጋር አካሂደዋል።
በዚሁ ወቅት ዶክተር መቅደስ ዳባ፤ አንድ ሥራ ሲያልቅ ለሀገር ልማት የሚሆን ሌላ ውጤት መፈለግ እንደሚገባ ከፕሮጀክቱ ሥራ መረዳታቸውን አብራርተዋል።
በኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት፣ ሀገራቸውን የሚወዱ ጠንካራ ባለሙያዎች መኖራቸውን ገልፀው፤ ፕሮጀክቱ ቅልጥፍና፣ ትጋት እና ውጤታማነት የታየበት ትልቅ ሥራ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ከዚህ በፊት ከፍተኛ ወጪ አስወጥተው ከውጭ ይገቡ የነበሩ ግብዓቶችን በራስ አቅም ማምረት የሚያስችል አቅም መፈጠሩን አንስተው፤ ይህን አቅም አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግም አመላክተዋል።
በቢታኒያ ሲሳይ