Search

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ የኃይል ቋት እየሆነች ነው - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ሰኞ ጥቅምት 17, 2018 115

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 2ኛውን የኢትዮጵያ ውኃ እና ኢነርጂ ሳምንትን ባስጀመሩበት ወቀት፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ የኃይል ቋት እየሆነች ነው ሲሉ ተናገሩ፡፡

በኢትዮጵያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከአየር ብክለት የፀዳ ኃይል ተጠቃሚዎች መሆናቸውን የተናገሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ በረከት ለኛ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት ሀገራት ወንድሞቻችን የተረፈ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ የኃይል ቋት እየሆነች ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በአሁኑ ሰዓት የታዳሽ ኃይል ለጅቡቲ፣ ለሱዳን እና ኬኒያ በሽያጭ እያቀረበች መሆኑንና በቅርቡም ወደ ሌሎች ሀገራት ይህንን ተግባር እንደምታስፋፋ ገልፀዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለው ይህ ልማት አጠቃላይ የኃይል ልማት ብቻ ሳይሆን የብልጽግና ጉዳይ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የዚህ የላቀ ህልም ማሳያ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ግድቡ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪካም ግድብ ነው ብለዋል።

ጎርፍን በመከላከል እና በታችኛው ተፋሰስ ላሉ ሀገራት ተገቢ የውኃ ተጠቃሚነትን በማሳደግ ለቀጣይ ከፉክክር ይልቅ የጋራ የተጠቃሚነት ህልምን ለመፍጠር የሚያስችል ስለመሆኑም አንስተዋል።  

በአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብር ኢትዮጵያ ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ እና ለዓለም መትረፍ የሚችል ስራ እየሰራች መሆኑን አንስተው፤ ከተተከሉት 48 ቢሊዮን ችግኞች መካከል አንድ ሶስተኛ የሚሆነው በዓባይ ተፋሰስ የተተከለ ስለመሆኑ ገልፀዋል፡፡

እያንዳንዱ ችግኝ ለምድራችን፣ ለጎረቤቶቻችን እና ለቀጣይ ትውልድ የተደረገ የትውልዳዊ ኃላፊነት ተግባር መሆኑን ያረጋግጥልናል ሲሉም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቅሰዋል፡፡

ኢኮኖሚያችን እያደገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የባህር በር ማግኘት ለነጋችን ዋስትና የሚሰጥ ነው ሲሉ የገለፁት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ልዩ ጥቅም የማግኘት ፍላጎት ሳይሆን መሰረታዊ ጥያቄ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ለዚህም ኢትዮጵያ ሰላማዊ፣ ዘላቂ እና የጋራ ተጠቃሚነትን የሚያሳድግ የባህር በር ለማግኘት በሚያስችል መልኩ ከጎረቤቶቿ ጋር በቅርበት እየሰራች ነው ብለዋል።

በአሸናፊ እንዳለ

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #GERD #Water #Energy