የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብሩ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የምትታወቅበት መገለጫ እየሆነ መጥቷል ሲሉ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ርስቱ ይርዳው ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች ለሰባተኛ ጊዜ "በመትከል ማንሰራራት" በሚል መሪ ሐሳብ እየተካሄደ በሚገኘው በአንድ ጀምበር 700 ሚልዮን ችግኝ የመትከል ሀገር ዓቀፍ መርሐ-ግብር ላይ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡
በዚህ ወቅት አቶ ርስቱ ይርዳው፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር አካባቢ መልሶ እንዲያገግም የሚከናወነው ሥራ የሀገራችን መገለጫ እየሆነ ነው ብለዋል ፡፡
ተቋሙ በተከታታይ በተደረጉት የችግኝ ተከላ መርሐ- ግብሮች ከፍተኛ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱን አመልክተዋል፡፡
አረንጓዴ አሻራ-መርሐ ግብር የተመጣጠነ ዝናብ እንዲኖር፣ ከተፈጥሮ ጋር ተስማምቶ ለመኖር እና በምግብ ራስን ለመቻል ትልቅ እገዛ የሚያደርግ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ዳይሬክተር ጄነራሉ፤ መርሐ- ግብሩ በየዓመቱ በተነሳሽነትና በንቃት የምንሳተፍበት እየሆነ ይገኛል ብለዋል።
አክለውም ባለፉት 7 ዓመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ አሻራ ተግባራት እንደ ሀገር በተጨባጭ የደን መመናመንን በማስቀረት ሽፋኑን ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ስር በሚገኘው የብሔራዊ ደኅንነት ዩኒቨርሲቲ በተካሄደው የችግኝ ተከላ መርሐ- ግብር፤ የአገልግሎቱ ምክትል ዳይሬክተር ጄነራሎች፣ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና ሠራተኞች ተሳትፈዋል፡፡