በ2018 የመጀመሪው ሩብ ዓመት የሳይበር ጥቃቶችን የመከላከል አቅሙን 97.8 በመቶ ማድረሱን የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) አስታወቀ።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ ኢመደአ የሳይበር ጥቃቶችን የመከላከል አቅሙን ከ99 በመቶ በላይ ከፍ ለማድረግ በትኩረት እንዲሠራ አሳስቧል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር የ2018 በጀት ዓመት የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምን ገምግሟል።

የኢመደአ ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት ሐሚድ የተቋሙን የአፈፃፀም ሪፖርት ሲያቀርቡ እንደገለጹት፥ በሩብ ዓመቱ 13 ሺህ 443 የሳይበር ጥቃቶች እና የጥቃት ሙከራዎች ተመዝግበዋል።
ከእነዚህ ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችሉ ከነበሩ 896 የሳይበር ጥቃቶች መካከል 874 ለሚሆኑት ምላሽ የተሰጠ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 22 ጥቃቶች በትንተና ሂደት ላይ ናቸው።
ይህ በኢትዮጵያ ላይ የተደረገው የሳይበር ጥቃት እና የጥቃት ሙከራ ባለፈው ዓመት ከተቃጣው ጋር ሲነፃፀር በእጅጉ መጨመሩን ወ/ሮ ትዕግስት ገልጸዋል።
የአስተዳደሩ የሳይበር ጥቃቶችን የመከላከል አቅም በ2018 የመጀመሪው ሩብ ዓመት 97.8 በመቶ መድረሱን ጠቅሰው፤ አሁንም አቅሙን ይበልጥ ለማሳደግ እየሠራ መሆኑን አክለዋል።
ኦፕሬሽናል ልህቀትን ከማሳደግ አንፃር፥ የ4 ተቋማት የሳይበር መከላከል የቅድመ ክፍተት ዳሰሳ፣ እንዲሁም በ6 ተቋማት ለሚገኙ 9 ሲስተሞች የ‘ኢቫሉዌሽን’ ሥራ መከናወኑን ወ/ሮ ትዕግስት ገልጸዋል።

በሩብ ዓመቱ፥ ለ4 የ‘ክሪፕቶ ማይኒንግ’ ቴክኖሎጂዎች ፈቃድ መሰጠቱን፣ ለ1 ተቋም (ፌዴራል ፖሊስ) ምዘና መከናወኑን፣ ለ5 ተቋማት የክላውድ አገልግሎት መሰጠቱን እና ለበርካታ ተቋማት እና ሲስተሞች የሳይበር ደኅንነት ፍተሻ ተደርጎ የተጋላጭነት ደረጃቸው መለየቱን ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂ በሀገር ውስጥ ከማልማት አንፃርም፥ ኤሮ-ዓባይ የድሮን ማምረቻ ተቋም በ300 ድሮኖች ምርት ሥራ መጀመሩን እና የኤሌክትሮኒክ ደረሰኝ አስተዳደር ሥርዓት የሶፍትዌር ሲስተም ተግባራዊ መደረጉን ገልጸዋል።
በሩብ ዓመቱ 166 ስጋት የሚፈጥሩ ቴክኖሎጂዎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ መደረጋቸውንም ዋና ዳይሬክተሯ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማህዲ (ዶ/ር) ሪፖርቱን ካዳመጡ በኋላ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ፥ ኢመደአ የሳይበር ጥቃቶችን የመከላከል አቅሙን 97.8 በመቶ ማድረሱን አድንቀው፤ ተቋሙ ይህንኑ የመከላከል አቅሙን ከ99 በመቶ በላይ ከፍ ለማድረግ በትኩረት እንዲሠራ አሳስበዋል።
ሁሉም ተቋማት ኢንተርኔት እንደሚጠቀሙ በማንሳትም አስተዳደሩ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በትብብር በመሥራት ሜጋ ፕሮጀክቶችን እና የፋይናንስ ተቋማትን ከሳይበር ጥቃት መከላለከል እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
በሞላ ዓለማየሁ
#ebcdotstream #ethiopia #insa #cybersecurity #cyberattack