ፀረ ባክቴሪያ ፣ ፀረ ቫይረስ እና ፀረ ፈንገስ የሆኑ ንጥረ ነገሮች በውስጡ እንደያዘ የሚነገርለት የኒም ዛፍ መድኃኒትንቱ ይበዛል።
ኒም ወይም Azadirachta indica በመባል የሚታወቀው ይህ ዛፍ በስፋት ጥቅሙ በተለመደበት በህንዳውያን ዘንድ ለሰዎች እና ለእንስሳት እንደ መድኃኒትነት ለተክሎች ደግሞ ፍቱን የፀረ-ተባይ መፍትሔ ሆኖ ለመቶ ዓመታት ሲያገለግላቸው ኖሯል።
ወባማ በሆኑ አካባቢዎች ደግሞ የዚህን ዛፍ ቅርፊት በማጨስ የወባ ትንኝን ከመኖሪያቸው ለማባረር ይጠቀሙበታል።
ስለ ዕፅዋት የሚያጠኑ ምሁራን የ21 ኛው ክፍለ ዘመን ዛፍ በማለት ይጠሩታል። እስከ 30 ሜትር ቁመትና 2.5 ሜትር ስፋት ማደግ የሚችለው ይህ ዛፍ ጉዳት ካልደረሰበት ከመቶ ዓመት በላይ መቆየት የሚችል ነው።
መሰረቱን በህንድና በአጎራባች ሀገራት አድርጎ መብቀል እንደጀመረ የሚነገርለት የኒም ዛፍ ከሚሰጠው ዘርፈ ብዙ ጥቅም የተነሳ ብዙ ሀገራት ወደሀገራቸው እየወሰዱ በማላመድ ላይ ናቸው።
ለዚህ ተክል ተስማሚ በሆነችው ኢትዮጵያም እንዲበቅል ማድረግ ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የዚህ ዛፍ ችግኝ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች እየተተከለ ይገኛል።
በኢትዮጵያም ለተለያዩ ጥቅሞች መዋል የጀመረው የኒም ዛፍን ቅጠል ሰብስበው በመውቀጥና ውሃውን የአትክልትና አዝዕርት እርሻዎች ላይ በመርጨት እንደ ፀረ-ተባይ ይጠቀሙበታል።
ከሚሰጠው ጥቅም የተነሳ በተለያዩ ሀገራት የተለያዩ ቅፅል ስሞች የሚታወቀው የኒም ዛፍ በሀገራችን “ክኒን” ዛፍ እየተባለ ሲጠራ በህንድ ደግሞ የገጠር መድኃኒት ቤት በማለት ይጠሩታል።
ህንድ ከዚህ ዛፍ ከሚሰሩ የተለያዩ ግብዓቶች በዓመት ከመቶ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ የምታገኝበት ሲሆን በአሁኑ ወቅት የተለያዩ የመድሀኒት ማምረቻ ካምፓኒዎች የኒም ዛፍ ዘይትን በሎሽን፣ በሳሙና፣ በክሬም፣ እና በሻምፖ ውስጥ በመጨመር ለውበት መጠበቂያ ምርቶቻቸው እንደ ዋና ግብዓት ይጠቀሙበታል።
በሀገራችንም የዚህን ዛፍ ችግኝ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ሲሰራጭ የነበረ ሲሆን ዛሬ ከሚተከሉት የዛፍ አይነቶች መሀከል ይህ የኒም ዛፍ ይገኝበታል።