Search

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ ያነሧቸው ሐሳቦች - ክፍል ሁለት

ማክሰኞ ጥቅምት 18, 2018 161

ሰላም እና ፀጥታን በሚመለከት

የኢትዮጵያን እድገት የማይሹ ሀገራት በጦርነት እንደማያሸንፉን ያውቁታል። ያላቸው ምርጫ ባንዳዎችን መላክ ነው። ኢትዮጵያን በቅጡ ያላወቁ የውስጥ ባንዳዎች ደግሞ ከጠላት ጋር በማበር ዓላማቸውን የሚያሳኩ ይመስላቸዋል። ይህ ፈጽሞ ሊሳካ አይችልም። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚያስፈልገው ብቻው መንገድ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ነው። መንግስት ችግሮች አሉኝ የሚሉ አካላት ጋር ቁጭ ብሎ በመነጋገር ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አሁንም በሩ ክፍት ነው።

የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ላይ የተቀመጡ ዋነኞቹ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? 

- ህወሓት ያካሄደው ምርጫ ሕጋዊ ምርጫ ባለመሆኑ መሰረዝ

- በትግራይ ክልል ሕጋዊ ባልሆነ ምርጫ የተቋቋመው የክልሉ አስተዳደር እና ምክር ቤት እንዲፈርስ

- ከሁሉም ወገን የተወጣጣ ጊዜያዊ አስተዳደር ማቋቋም

- በሕዝብ የተመረጠውን የፌዴራል መንግሥት ሥርዓት ማክበር

- በክልሉ ታጥቀው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ኃይሎች ትጥቅ መፍታት እና በተሃድሶ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው መመለስ

- የተቋረጡ አገልግሎቶችን ወደ ሥራ ማስመለስ

- ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መመለስ

- የትኛውም የውጭ ግንኙነት የማከናወን ሥልጣን ያለው የፌዴራል መንግሥቱ ብቻ መሆኑን ማክበር የሚሉት ናቸው።

በትግራይ ክልል ያለውን የሰላም ሁኔታ በሚመለከት

በትግራይ ክልል ተጨማሪ ወጊያ እንዲካሄድ አንፈልግም። ከዚያ ይልቅ ተባበረን ሀገር ማልማት ነው የምንፈልገው። ከዚያ ውጭ መንግስትን በሃይል ለመጣል ፍላጎት ካለ እሱ ፈጽሞ ሊሳካ አይችልም። የፌደራል መንግስት ለትግራይ ክልል የሚመድበው በጀት ለልማት ሳይሆን ለታጣቂ  እየዋለ ነው። ይህ ትክክል አይደለም። ትግራይ ልማት ያስፈልጋታል። በመሆኑም በሰላማዊ መንገድ በትብበር ለልማት መስራት ይገባል።

7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በተመለከተ

ምርጫውን ለማከናወን መንግስት በቂ አቅምና ዝግጁነት አለው። 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ እስካሁን በኢትዮጵያ ከተካሄዱ ምርጫዎች የተሻለ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ምርጫው ዴሞክራሲያዊና ብዘሃ ድምጾች ያሉት እንዲሆን በሃላፊነት እንሰራለን። እኛ እንደ ፓርቲም፤ እንደ መንግስትም ዝግጁ ነን። ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከወዲሁ መዘጋጀት አለባቸው።

ተቋማዊ ሪፎርም በሚመለከት

በአገልግሎት አሰጣጥ ያለውን እንግልት ለመቀነስ የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሀገር አቀፍ ደረጃ እይሰፋ ነው። አሁን ላይ 18 ማዕከላት አገልግሎት እየሰጡ ነው። ሶስት ማዕከላት ደግሞ በቅርቡ ስራ ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል። በተያዘው በጀት ዓመትም ይህን ቁጥር ወደ 100 ለማድረስ እየተሰራ ነው። ይህም በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚያመጣ ይጠበቃል።

ዲጂታላይዜሽንን በሚመለከት

ኢትዮጵያ ውስጥ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ወጣቶች በነጻ የኮዲንግ ስልጠና ወስደዋል። ይህ ትልቅ ቁጥር ነው። 93 ሚሊዮን ደንበኞች ደግሞ የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚ ሲሆኑ 55 ሚሊዮን ዜጎች ደግሞ የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ይህ ኢትዮጵያን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የጀመረነው ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ለውጥ እያመጣ መሆኑን አመላካች ነው።

የዓባይ ውሃ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን በሚመለከት

ኢትዮጵያ በብሔራዊ ጥቅሟ ላይ -ፍትሃዊና -ርታዊ ውሳኔ የተወሰነባት ሀገር ናት። ዓባይን መጠቀም ተፈጥሯዊና ህጋዊ መብቷ ነው። ሃብቱም በጋራ ለመጠቀም በቂ ነው። ኢትዮጵያ አሁንም ያላት አቋም ግልጽ ነው። ግብጻዊያንም ሱዳናዊያንም ወንድሞቻችን ናቸው። ስለዚህ የሚያዋጣው በመነጋገርና በመተባበር በጋራ ማደግ ነው። እኛ ማንንም በሚጎዳ መልኩ አናቅድም አንሰራም።

ቀይ ባህርን በተመለከተ

የቀይ ባህር ጉዳይ ህጋዊ፣ ታሪካዊ፣  መልከዓ ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ነው ብለን እናምናለን። ይህንን በተረጋጋ መንገድ ማየት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያን የቀይ ባህር የማጣት ውሳኔ ማን ወሰነ ብለን ስንፈልግ ተቋማት አልገቡበትም። ይህን የሚያህል የህልውና ጉዳይ ማን እንደወሰነ መጠየቅ ተገቢ ነው። ኢትዮጵያ ተዘግቶባት መኖር አትችልም። ለጎረቤቶቻችን መናገር የምንፈልገው ኢትዮጵያ ስታደግ ለቀጣናውም ልማት ምንጭ ትሆናለች። የምንፈልገው በትብብር ማደግ ነው።

#የጠሚሩምላሾች #PMOEthiopia #EBC #ebcdotstream #Ethiopia #corridordevelopment