የቼዎንጄቼዎን ወንዝ የደቡብ ኮሪያ ዋና ከተማ ሴዑልን አቋርጦ የሚሄድ ንፁህና ዳርቻዎቹ በአረንጓዴ ተክሎች የተዋበ ወንዝ ነው።
ይህ ወንዝ ከመቶ ዓመታት ጀምሮ ከተማዋን አቋርጦ የሚያልፍ የነበረ ሲሆን በአንድ ወቅት ግን ሙሉ ለሙሉ በኮንክሪት ተደፍኖ የመኪና መንገድ እንዲሆን ተደርጎ ቆይቷል።
ትልቅ የመኪና መንገድ ተሰርቶበት ለሰላሳ አመታት የጠፋው ወንዝ ግን ተመልካች አገኘ::
ለከተማዋ ውበትና ለአካባቢ ጥበቃ ወሳኝ እንደሆነ በመታመኑ በላዩ ላይ ተገንብቶበት የነበረው የመኪና መንገድ ፈርሶ ወንዙ እንደገና በከተማ እንዲፈስ ተደረገ።
ይህ ዓለምን ያስደነቀውና ለአካባቢ ጥበቃና ልማት ለከተማ ውበት ሲባል እውን የሆነው አስገራሚ የግንባታ ሂደት ምን ይመስል ነበር? ወንዙን በኮንክሪት ለመሸፈን የተፈለገበት ምክንያትስ ምንድን ነው? በዝርዝር እንየው::
በ1950ዎቹ እና 1960ዎቹ ውስጥ ደቡብ ኮሪያ ለዘመናት ከነበረችበት ከባድ ድህነት ለመላቀቅ ብዙ ሥራ የሰራችበት ሆኖ ይታወሳል::
የህዝቧን ህይወት ለመለወጥ የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ነድፋ ወደስራ የገባችው ደቡብ ኮርያ ኢኮኖሚዋ መነቃቃት የጀመረችበት ወቅትም ነበር።
ይህም በከተማዋ መታየት የጀመረውን ፈጣን የኢኮኖሚ አድገት ለማስተናገድ ትላልቅ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች ያስፈልጉ ነበር።
ከነዚህም መካከል የትራፊክ ፍሰቱን ለማቀላጠፍ የሚጠቅም የመንገድ መሰረተ ልማት አንዱ ሆነ።
በተለይ በዋና ከተማዋ ሴኦል ያለው የትራፊክ መጨናነቅ በቶሎ መፍትሄ የሚፈልግ በመሆኑ ትልቅ አውራ ጎዳና ለመገንባት ጥናት መካሄድ ጀመረ።
የጥናቱን ውጤት ይዘው የቀረቡት ባለሙያዎች የከተማዋን የትራፊክ መጨናነቅ ያስወግዳል ብለው የወሰኑት 11 ኪሎ ሜትር የሚረዝመውንና ከተማዋን አቋርጦ የሚያልፈውን ወንዝ ሙሉ ለሙሉ በኮንክሪት በመድፈን ወደ መሬት ከለወጡ በኋላ በዛ ላይ መንገድ መስራት የሚል ሆነ።
የቼዎንጄቼዎን ወንዝ በወቅቱ የከተማዋ የፍሳሽ ማስወገጃ ሆኖ ያገለግል ስለነበር በከፍተኛ ሁኔታ ተበክሏል::
እናም ይህን ወንዝ አፅድቶ ከመጠበቅ ይልቅ በወቅቱ ባለው ግንዛቤ ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ለኢኮኖሚ ልማት ነው ብለው ተፈጥሮን ለኢኮኖሚ ጥቅም መስዋዕት አደረጉ::
ለዘመናት ሲፈስ የነበረውን የቼዎንጄቼዎን ወንዝን በኮንክሪት ደፍነው ከላይና ከታች መኪኖችን የሚያሳልፍ ትልቅ የአስፓልት መንገድ ተገነባ።
ወንዙን በኮንክሪት ለመድፈን ብቻ ሶስት ዓመታትን ሲወስድ በተደፈነው ወንዝ ላይ ዘመናዊ መንገድ ለመገንባትም በርካታ ዓመታት አስፈልጓል።
በዚህ መልኩ በዘመናዊ የፍሳሽ ማስወገጃ ዘዴ ተተክቶ ሙሉ ለሙሉ የተደፈነው የቼዎንጄቼዎን ወንዝ ለምልክት እንኳን ሳይቀር የመኪና መንገድ ሆኖ ሰላሳ ዓመታት አልፏል።
ይህ ከሆነ ከዓመታት በኋላ ግን የሀገሪቱ አቅም እያደገ ከበለፀጉ ሀገራት ተርታ መሰለፍ ስትጀምር ደቡብ ኮሪያ የተሸፈነው ወንዝ ፈለገች::
ወንዙ በሚገባ አምሮና ፀድቶ በከተማው መሀከል ቢኖር የከተማዋን ገፅታ ከመቀየርም ባሻገር ለስነምህዳሩ ትልቅ አስተዋፅኦ እንደሚሰጥ ማሰብ ጀመሩ።
አስበውም አልቀረም ከብዙ ዓመታት በፊት የነበረውንና በኮንክሪት ተደፍኖ ወደ አስፓልትነት የተቀየረውን የቼዎንጄቼዎን ወንዝ ዳግም ህያው ለማድረግ ወደስራ ገቡ።
በዚህም መሰረት በላዩ ላይ የተገነባው መንገድ ማፍረስ እና በወንዙ ላይ የተደመደመውን ኮንክሪት ማውጣት ተጀመረ።
ይህ የከተማዋን ገፅታ ሙሉ ለሙሉ የሚቀይር ሀሳብ ለመተግበር በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ቢያስፈልግም ኮርያውያን ቆርጠው ገቡበት።
በዚህ መልኩ የከተማዋን ዋና አውራ ጎዳና በማፍረስ ለዓመታት ተቀብሮ የኖረውን ወንዝ ለመመለስ የተጀመረው ፕሮጀክት 380 ሚሊዮን ዶላር ወጭ ተመድቦለት በተጀመረ በ27 ወራት ውስጥ ተጠናቀቀ።
ይህ ከተማዋን አቋርጦ የሚያልፈውና በአረንጓዴ ዳርቻዎች የተዋበው ወንዝ የዋና ከተማዋን የሴዑልን ውበት በአስገራሚ ሁኔታ ከመቀየሩም በላይ ለአየር ንብረትና ለአካባቢ ጥበቃ የሰጠው አስተዋፅኦ ትልቅ ነበር።
በዚህም መሰረት ወንዙ ዳግም ህያው ከሆነ በኋላ በአካባቢው ያለውን የሙቀት መጠን አስከ 5° C አንዲቀንስ በማድረግ ለከተማዋ ተፈጥሯዊ የአየር ማቀዝቀዣ መሆን ችሏል።
ከዓመታት በፊት በኮንክሪት ተቀብሮ የመኪና መንገድ የነበረው የቼዎንጄቼዎን ወንዝ የሴኡል ነዋሪዎችና ቱሪስቶች የሚዝናኑበት እና ከከተማ ግርግር እረፍት የሚያገኙበት ውብ ማዕከል ሆኗል።