ሉሲና ሰላም ከሁለት ወር የፕራግ ሙዚየም ቆይታ በኋላ ወደ ሀገር ቤት ተመለሱ።
ሉሲና ሰላም በቼክ ሪፐብሊክ ፕራግ ሙዚየም የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ዛሬ ንጋት ላይ አዲስ አበባ ገብተዋል።
በቆይታቸውም ከመላው አውሮፓ በጎረፉ ቱሪስቶች የተጎበኙ ሲሆን፤ የኢትየጵያን የሰው ዘር መገኛነት በማሳየት እና የጥንታዊ ስልጣኔ ባለቤትነት በዓለም አደባባይ በማስተዋወቅ የኢትዮጵያን ገጽታ ከፍ የማድረግ ሚናን በላቀ ሁኔታ መወጣታቸውን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሉሲና ሰላም ከፕራግ ወደ አዲስ አበባ ጉዞ በቅርስ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው የተመራ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የቼክ አምባሳደርን ጨምሮ በፕራግ ሙዝየም አመራሮች እና የሀገሪቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም ታጅበዋል።
በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለማቀፍ አየር ማረፍያ በመገኘት የቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ስለሺ ግርማ እና የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል።