Search

አለአግባብ የፈረሰው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል እና በብረታ ብረት ዋጋ ተቆራርጠው የተሸጡት የጦር መርከቦች

ረቡዕ ጥቅምት 19, 2018 3049

“USS Orca” በ1962 (እ.አ.አ) በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በነበሩት ጆን ኤፍ ኬኔዲ ለኢትዮጵያ መንግሥት እስከተሰጠችበት ጊዜ ድረስ በአሜሪካ ባሕር ኃይል ሥር የነበረች እና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተሳተፈች በወቅቱ ዘመናዊ የምትባል የጦር መርከብ ነበረች።

ይህች ግዙፍ መርከብ ለኢትዮጵያ መንግሥት ከተሰጠች በኋላ “ኢትዮጵያ A-01” የሚል ስያሜ ተሰጥቷት በ1958 አዲስ በተቋቋመው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ንብረት ሆና የደርግ መንግሥት እስኪወድቅ ድረስ ስታገለግል ቆይታለች።

በኢትዮጵያ ከተፈጠረው የሥርዓት ለውጥ ጋር ተያይዞም ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል “ኢትዮጵያ A-01” እና ሌሎች የኢትዮጵያ መርከቦች መጠጊያ ፍለጋ ወደ የመን እና ሳዑዲ ዓረቢያ ወደቦች ተጉዘው በዚያ ለመቆም ተገደዱ።

ሆኖም ከዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ታሪክ ግዙፍ የነበረችው “ኢትዮጵያ A-01” የጦር መርከብ፣ የመጨረሻ ዕጣ ፈንታዋ እንደማያገለግል ዕቃ ተቆራርጦ ወደ ብረትነት ተቀይሮ በኪሎ መሸጥ ሆነ።

በዚያን ወቅት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል 26 ያህል የተለያዩ የባሕር ኃይል መርከቦች የነበሩት ሲሆን ብዙዎቹ በየመን፣ በኋላም በጂቡቲ ለዓመታት ቆመው ነበር።

በ1958 የተቋቋመው እና እስከ 1990 ድረስ የቆየው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ትልቅ ስም የነበረው እና በሠለጠኑ ባለሙያዎች የተዋቀረ ጠንካራ የመከላከያ ኃይል ነበር።

3 ሺህ 500 የሚሆኑ በውጭ ሀገራት እና በሀገር ውስጥ የሠለጠኑ የባሕር ኃይል አባላትን ያቀፈው ይህ የቀድሞው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ፡ ከአሜሪካ ኖርዌይ ስዊድን እና ጀርመን በስጦታ እና በግዢ የተገኙ የተለያዩ መርከቦች እና ትላልቅ የጦር ጀልባዎች ነበሩት።

ባሕር ኃይሉ በደርግ ዘመን ከሩሲያ የተገዛችውን “የካቲት 66” (ኦሳሱ) የሚል ስያሜ ያላትን ሚሳኤል ተኳሽ መርከብን ጨምሮ ከ26 በላይ የጦር መርከቦች ነበሩት።

የቀድሞው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ስምንት ሚሳኤል ተኳሽ እና ስድስት ተምዘግዛጊ ቶርፒዶ ሚሳኤል የታጠቀ ሲሆን ሌሎቹም የቅኝት የውጊያ የልምምድ እና ለተመሳሳይ ጉዳዮች የሚያገለግሉ የጦር መርከቦች ነበሩት።

ከነበሩት መርከቦች መካከል ደግሞ “ኢትዮጵያ A-01” ትልቋ ነበረች። ይህች ንብረትነቷ የአሜሪካ የነበረ እና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ተሳትፋ ትልቅ ዝና ያገኘች መርከብ በ1962 በአሜሪካን መንግሥት ለኢትዮጵያ በስጦታ የተበረከተች ነበረች።

ኢትዮጵያ በወቅቱ በተለያዩ ሀገራት እና በሀገር ውስጥ በሠለጠኑ ዘመናዊ የባሕር ኃይል አባላት፣ አመራሮች እና የተጠቀሱ መርከቦችን በማካተት ጥሩ ስም እና ዝና የነበረው የባሕር ኃይል ለማቋቋም ችላ ነበር።

ሆኖም በ1990 የደርግ ሥርዓት ማብቃትን ተከትሎ በሚገባ ተደራጅቶ የነበረው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ኅልውና ጥያቄ ውስጥ መግባት ጀመረ።

ይህን ተከትሎም የኤርትራ ኃይሎች የምፅዋ እና የአሰብ ወደቦችን ሲቆጣጠሩ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል የጦር መርከቦች ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ እና የመን ወደቦች ለመሰደድ እና በዚያ ለመቆየት ተገደዱ።

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ከነበሩት 26 የተለያዩ ዓይነት መርከቦች መካከል በአሰብ ወደብ ላይ እያሉ ከወደሙት ጥቂት መርከቦች ውጭ በአብዛኛው ከጥቃት ተርፈው ነበር።

እነዚህ የኢትዮጵያ መርከቦች ከሀገር ተሰድደው ከሄዱ ከሁለት ዓመታት በኋላ ግን የየመን መንግሥት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል መርከቦች ግዛቷን ለቅቀው እንዲወጡ ጠየቀ።

“ኢትዮጵያ A-01” እና ሌላ አንድ መርከብ በዚያ ሲቀሩ ሌሎቹ የየመንን ወደብ ለቅቀው ወደ ጂቡቲ ወደብ አመሩ። ከመርከቦቹ ጋር ወደ የመን የተሰደዱ 200 ኢትዮጵያውያን መርከበኞችም በዚያው ቀርተዋል።

ትልቋ የባሕር ኃይል መርከብ “ኢትዮጵያ A-01” በየመን ወደብ ለዓመታት ከቆየች በኋላ በ1993 በብረታ ብረት ዋጋ ተቆራርጣ እንድትሸጥ ተፈረደባት።

ከዚህች ግዙፍ መርከብ በተጨማሪም በየመን ወደብ ቆመው የነበሩት ሌሎች የባሕር ኃይል መርከቦች መለዋወጫቸው እየተፈታ በተመሳሳይ መልኩ እንዲሸጡ ተደረገ።

ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የተጓዙት ጥቂት መርከቦች ዕጣ ፈንታም ከዚህ የተለየ አልሆነም። ከዚህ በኋላ በየመን ወደቦች የነበሩት እና በ1993 ወደ ጂቡቲ ወደብ የተጓዙት አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ መርከቦች በጂቡቲ ወደብ ለዓመታት ቆመው ነበር።

ሆኖም የጂቡቲ መንግሥት መርከቦቹ ለዓመታት የቆሙበትን የወደብ ኪራይ የሚከፍለኝ አጥቻለሁ በማለት በ1996 በዚያ ቆመው የነበሩትን የኢትዮጵያን የባሕር ኃይል የጦር መርከቦች ለመሸጥ እንደወሰነ በይፋ አስታውቆ መርከቦቹን እና የባሕር ኃይል ጀልባዎቹን ለመሸጥ ጨረታ አወጣ።

በዚያው ዓመትም የኢትዮጵያ መንግሥት አዲስ አበባ የሚገኘውን የባሕር ኃይል ዋና መሥሪያ ቤት በመዝጋት የ41 ዓመታት የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ጉዞ በዚያው ተገታ።

ይህንን ተከትሎም የኤርትራ መንግሥት በዚያ የነበሩትን 16 የሚደርሱ መርከቦች እና ጀልባዎችን የመግዛት ፍላጎት እንዳለው የገለጸጸ ቢሆንም፣ ኋላ ላይ ሩሲያ (ሶቪየት) ሠራሽ የሆነችውን Osa-II ሚሳኤል ተሸካሚ የባሕር ኃይል ጀልባን ጨምሮ አራት መርከቦች ብቻ እንደተሸጡለት ታውቋል።

የተቀሩት የባሕር ኃይል መርከቦችም ግማሾቹ እንዳሉ የተቀሩትም በብረታ ብረት መልክ እየተቆራረጡ ተቸበቸቡ።

የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ትንሣኤ ጅማሮ

ከላይ በዝርዝር በተጠቀሰው መሠረት አለአግባብ እንዲዳከም እና እንዲፈርስ የተደረገው የ41 ዓመታት ታሪክ የነበረው የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ታሪክ በ1996 (እ.አ.አ) በይፋ እንዲዘጋ ተደርጎ ኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ከሌላቸው ሀገራት ዝርዝር ውስጥ ተካተተች።

ሆኖም ከለውጡ በኋላ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ትዕዛዝ የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ዳግም እንደ አዲስ እንዲቋቋም ተደርጓል።

በዚህም በሩሲያ እና በሌሎች ሀገራት የባሕር ኃይል አባላትን የማሠልጠኑ ሥራ በስፋት ተከናውኗል።

በሀገር ውስጥም የማሠልጠኛ ተቋም እና የማዛዣ ጣቢያ ተከፍቶ የኢትዮጵያን የባሕር ኃይል ዳግም ኃያል ለማድረግ እየተሠራ ነው።

ለዚህ ጽሑፍ ግሎባል ሴኪውሪቲ፣ ዋር ሰርቸር ዶትኮም እና የሪቮልቪ ዶትኮምን እንደምንጭነት ተጠቅመናል።

 

በዋሲሁን ተስፋዬ

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #ethiopiannavy #navy