Search

በፕራግ ሙዚየም ታሪክ በአጭር ጊዜ በብዛት የተጎበኘው የሉሲና ሰላም ኤግዚቢሽን

ረቡዕ ጥቅምት 19, 2018 69

ላለፉት ሁለት ወራት በቼክ ርዕሰ መዲና ፕራግ በሚገኘው ብሔራዊ ሙዚየም ለእይታ ቀርበው የነበሩት የሉሲና ሰላም ቅሪተ-አካላት ኤግዚቢሽን በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት የሳበና ከ200 ሺ ሕዝብ በላይ የጎበኘው ሆኗል።
በፕራግ ሙዚየም ታሪክ እጅግ ስኬታማ ከሆኑ ኤግዚቢሽኖች ዋናው ለመሆንም ችሏል።
በሁለት ወራት ውስጥ ይህን ያህል ጎብኚ የነበረው ኤግዚቢሽን እንዳልነበረ ተገልጿል።
ቅሪተ አካላቱ ለሕዝብ እይታ ከቀረቡበት እለት አንስቶ ለመጎብኘት የሚመጡት ሰዎች ቁጥር በመብዛታቸው ብሔራዊ ሙዚየሙ የሥራ ሰዓቱን በመጨመር እንዲሁም የጊዜ ገደብ ያላቸውን ቲኬቶች (Timed-entry tickets) በማዘጋጀት ሰዎች በተያዘላቸው የጉብኝት ሰዓት ብቻ እንዲጠቀሙ አድርጓል።
 
በዚህም አሰራር ሙዚየሙ ከፍተኛ የነበረውን የጎብኚዎች ፍላጎት ለማስተናገድ መሞከሩ ተገልጿል።
በተጨማሪም የሉሲንና ሰላምን ቅሪተ-አካላት ወደ ቼክ ሪፐብሊክ ሙዚየም መምጣቱን በማስመልከት ለመታሰቢያ የሚሆኑ የተለያዩ እቃዎች ለገበያ ቀርበው የነበረ ሲሆን፣ እነዚህ በውስን መጠን የተዘጋጁ የመታሰቢያ ዕቃዎችን ለመግዛት የነበረው ፍላጎትም ከፍተኛ ነበር ተብሏል።
ይህን ታሪካዊ ጉብኝት ለማሰብ በሙዚየሙ ከተዘጋጁት የመታሰቢያ እቃዎች መካከል የሉሲ ምስል የታተመባቸው ቲሸርቶች እንደመጠናቸው ከ14 እስከ 23 ዶላር ተሸጠዋል።
በተጨማሪ የሸራ ቦርሳ 12 ዶላር እንዲሁም የቁልፍ መያዣዎች ስድስት ዶላር ዋጋ ወጥቶላቸው ሲሸጡ እንደነበርም ተገልጿል።
የሉሲና ሰላም ቅሪተ-አካላት በቼክ ሪፐብሊክ የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ዛሬ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰዋል።
ይህ ጉዞ ኢትዮጵያን በማስዋወቅ ረገድ ውጤታማ ሥራ የተከናወነበት መሆኑም ተገልጿል።
 
በዋሲሁን ተስፋዬ