Search

የኢትዮጵያ ተሳትፎ በ3ኛው የአፍሪካ የመሠረተ ልማት ፋይናንስ ጉባዔ

ዓርብ ጥቅምት 21, 2018 69

ኢትዮጵያ በአንጎላ ርዕሰ መዲና ሉዋንዳ በተካሄደው 3ኛው የአፍሪካ የመሠረተ ልማት ፋይናንስ ጉባዔ ላይ ተሳትፋለች።
በጉባዔው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና የፋይዳ የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ተወካዮችን የያዘ የልዑካን ቡድን ኢትዮጵያን ወክሎ ተሳትፏል።
የጉባዔው ዋና ትኩረት ለአጀንዳ 2063 ሁለተኛው የአስር ዓመት የትግበራ እቅድ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶች የሚውል ሃብት ማሰባሰብ ላይ ነው።
በመድረኩ አፍሪካን በሚያስተሳስሩ የአየር ትራንስፖርት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ገበያ፣ የውሃና ንፅህና ፕሮጀክቶች ፋይናንስ እንዲሁም የባቡር መስመር ፕሮጀክቶች ላይ ውይይት ተደርጓል።
ኢትዮጵያ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ የአየር መንገድ ፕሮጀክቶች እና የኢትዮ-ጅቡቲ የባቡር መስመር ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶቿ በመሰረተ ልማት ግንባታ ረገድ አርዓያ ሆነው በጉባዔው ቀርበዋል።
ጥናቶች እንዳመለከቱት የአፍሪካ የመሠረተ ልማት የፋይናንስ ክፍተትን ለመሙላት የጡረታ ፈንድን፣ ሉዓላዊ የሀብት ፈንድን እና የንግድ ባንኮችን በማስተባበር ወደ 4 ትሪሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብን ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል።
የጉባኤው ውጤት በ39ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል ሲል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል።