ቀለመ ብዙ ሕብረ ብሔራዊነት መገለጫው የሆነው ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ወላይታ ሶዶ የክልሉ የፖለቲካ እና የአስተዳደር ማዕከል ሲሆን፣ በዲላ፣ አርባ ምንጭ፣ ሳውላ፣ ካራት እና ጂንካም የተለያዩ የክልል ቢሮዎች ተቋቁመዋል።
የበርካታ ብሔሮች የጋራ መኖሪያ የሆነው ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ልዩ የሆነ ማኅበራዊ እና ባህላዊ እሴቶች የሚገኙበት የኢትዮጵያ ብዝኃነት ማሳያ ነው፡፡
እንደ ደቡብ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ በክልሉ 32 ብሔሮች በኅብረ-ብሔራዊ መሠረት ላይ የታነፀውን ጠንካራ አንድነታቸውን አጽንተው በሰላም እና በፍቅር የሚኖሩበት ክልል ነው፡፡
ክልሉ የኅብር ማንነቶች፣ የበርካታ ውብ ቱባ ባህሎች፣ የድንቅ የተፈጥሮ መስህቦች፤ የማራኪ መልክዓ ምድር እና ሌሎች በርካታ ፀጋዎች ባለቤት ነው፡፡
የድንቅ ትውፊቶች፣ ባህሎች እና ማኅበራዊ እሴቶች ባለቤት የሆኑት የክልሉ ህዝቦች ዘመን በተሻገረ አብሮነት እና የእርስ በእርስ መስተጋብር በፍቅር የተጋመዱ የውበት እና ጥንካሬ አብነቶች ናቸው፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የብዝኃ ህዝቦች እና ባህሎች መገኛ ብቻ ሳይሆን እምቅ የቱሪዝም መስህቦችና ፀጋዎች ባለቤትም ጭምር ነው፡፡
ውብ ባህሎች፣ አስደናቂ መልክ ዓምድር፣ ድንቅ ተፈጥሮ፣ ብዝኃ ሕይወት፣ ጥብቅ ደኖች እና ፓርኮች፣ እንዲሁም የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ሃይማኖታዊ እና ታሪካዊ ቦታዎች እና ሌሎች የቱሪስት መዳረሻዎች ናቸው።
ለኑሮ አመቺ የሆነው ክልሉ በግብርና፤ በአገልግሎት፤ በኢንዱስትሪ እና ሌሎችም ዘርፎች እምቅ አቅም ያለው እና ማንም ሰው በላቡ ያፈራውን አፍሶ የሚኖርበት ነው፡፡
ከከልሉ ዞኖች አንዱ ጋሞ ጎፋ የአስታራቂዎቹ ጋሞዎች ምድር፣ ዓባያ፣ ጫሞ ሐይቆች የሚገኙበት ሲሆን፣ ነጭ ሣር ብሔራዊ ፓርክ የሚገኝበት ነው።
ጊፋታ የተባለ የራሱ የዘመን አቆጣጠር፣ ምቹ የአር ንብረት እንዲሁም የጥንት ነገሥታት ምድር የሆነው ወላይታ ከክልሉ ውበቶች መካከል አንዱ ነው፡፡
በጥንቱ የገዳ ሥርዓት የሚተዳደሩት እና የይርጋ ጨፌ ቡናን ለዓለም የሚበረክቱ ጌዴኦዎች በክልሉ የሚገኙ ናቸው፡፡
ብዝኃ ባህል እና ቋንቋዎች ስብጥር የሚታወቀው ደቡብ ኦሞ ለሥነ-ልሳን ተመራመሪዎች ግብዓት የሚሆኑ ቋንቋ ቤተሰቦች ባለቤት ነው።
የተጣላ ሳይታረቅ የማይከበረው አዲስ ዓመት ድሽታ ግና ባለቤቶች የሆኑ የአሪ ብሔር መገኛም ነው ደቡብ ኢትዮጵ ክልል፡፡
ድንጋያማ፣ ደረቅ፣ ተራራማ እና ወጣ ገባ የሆነውን መሬት በባህላዊ መንገድ እርከን እየሠሩ እና እያረሱ አፈሩ እንዳይሸረሸር በማድረግ ውጤታማ የሆነ ማኅበረሰብ መገኛም ነው ክልሉ፡፡
ኮንሶዎች በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃቸው ዓለም አቀፍ እውቅናን አግኝተው በዩኔስኮ ተመዝግበዋል።
የዓድዋ ታሪክ በአካል የሚዳሰስባት እንዲሁም በኅብረ-ዜማ የደመቀች፣ በኪነ-ጥበብ እና በታሪክ ያበበች ጥንታዊቷ ከተማ ጊዶሌ የክልሉ ሌላኛዋ ድምቀት ነች፡፡
በቡራ ቡርጂ ቦሎቄ እና ማኛ የቡርጂ ጤፍ በማምረት የምትታወቀው ቡርጂ ሌላኛው የክልሉ እና የኢትዮጵያ በረከት ነች።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ስቱዲዮ የተጨማሪ ይዘት ምንጭ ስቱዲዮ ከከፈተባቸው ክልሎች መካከል ይህ በተፈጥሮም በታሪክም በታደለው ክልል ይገኝበታል፡፡
መረጃን ከሕዝብ የሚያደርሰው ኢቢሲ በክልሉ ያለውን ብዝኃ ባህል ከታሪክ እንዲሁም የተፈጥሮ ሀብት ለመላው ኢትዮጵያ ለማስተዋወቅ ነው ስቱዲዮውን በወላይታ ሶዶ የከፈተው፡፡
በሁሉም የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ተጨማሪ የይዘት ምንጮችን በማስፋት ወቅታዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮችን በጥልቀት እየተነተነ ጠንካራ፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ሀገራዊ ጥረት ውስጥ የድርሻውን ለመወጣት ከምንጊዜውም በላይ በትኩረት እየሠራ መሆኑ ይታወቃል፡፡
#EBC #ebcdotstream #ኢቢሲወደይዘት #southethiopia #wolaitasodo