Search

ዜጎችን በፍትሐዊና አካታች መንገድ ተጠቃሚ የሚያደርጉት የልማት ሥራዎች

ማክሰኞ ጥቅምት 25, 2018 45

ፍትሐዊና አካታች ልማቶች የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ወሳኝ ሚና አላቸው። በርካቶችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ መሠረተ ልማቶችን እና ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን በማስፋፋትም የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ውጤትን ማስመዝገብ ይቻላል።
በአዲስ አበባ እና በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተገነቡ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የዜጎችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድ ማሳያ መሆን እንደሚችሉም ይገለጻል።
 
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ መምህር እንዲሁም የፕሮ ኢንቨስት ካፒታል መሥራች የሆኑት አቶ አየለ ከበደ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ኢትዮጵያ ዘላቂና አካታች ፍትሐዊ ልማትን በመገንባት የጀመረቻቸው ሥራዎች ተስፋ ሰጪ ለውጦችን እያሳዩ መሆኑን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ ፍትሐዊና አካታች ልማትን እየፈጠረች መሆኑን የጠቀሱት አቶ አየለ፣ በዚህ ረገድ የኮሪደር ልማት፣ ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች እና የኢኮ ቱሪዝም ሥራዎች ለአብነት ተጠቃሽ እንደሆኑ አንስተዋል። እነዚህም ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱም ገልጸዋል።
ልማቶቹ አንድ አካባቢን ብቻ ያማከሉ ሳይሆኑ የሁሉንም አካባቢ ኅብረተሰብ ተጠቃሚ ያደረጉ መሆናቸውንም ነው ያስረዱት።
በተጨማሪም በመንግሥት ብቻ የተያዙ ተቋማት እና ዘርፎችን ለግል ዘርፉ ክፍት በማድረግ ዜጎችን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን አንስተው፤ ይህም ፍትሐዊና አካታች ልማትን ለማሳደግ አይነተኛ መንገድ መሆኑን አመላክተዋል።
በቀጣይም የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በማስፋፋት ፍትሐዊና አካታች ኢኮኖሚን ማጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል።
 
በሜሮን ንብረት