Search

ከሕክምና በተጓዳኝ በመንፈስ ጥንካሬዋ የጡት ካንሰርን አሸንፋ ሌሎችን በማገዝ ላይ የምትገኘው ቬሮኒካ

ሓሙስ ጥቅምት 27, 2018 38

ቬሮኒካ ሙሴ ኑሮዋን በሀገረ አሜሪካ አድርጋ ለበርካታ ዓመታት ኖራለች።

ቬሮኒካ ሦስተኛ ልጇን ከወለደች በኋላ ጡቷ ላይ ፈሳሽ ማስተዋል ብትጀምርም፤ ጉዳዩን ከወሊድ እና አራስነት ጋር የተያያዘ እንደሆነ በማሰብ ወደ ሕክምና ተቋም ሳትሄድ ጊዜያት ያልፋሉ።

ሕመሙ ሲበረታባት ወደ ሕክምና ተቋም ሄዳ ትመረመራለች፤ እናም የጡት ካንሰር እንዳለባት ይነገራታል።

ይህን ከሰማች በኋላም ሕክምናውን አድርጋ ከሕመሟ ከዳነች ተመሳሳይ ሕመም ያጋጠመውን አንድም ሰው ቢሆን ለመርዳት ለራሷ ቃል ትገባለች።

የካንሰር ሕክምና አድርጋ ከሕመሟ ማገገሟን ተከትሎ እአአ በ2013 ዓ.ም አልፋ ብሬስት ካንሰር የተሰኘ ለትርፍ ያልቋቋመ ድርጅት ትከፍታለች።

አልፋ ብሬስት ካንሰር ባለፉት ዓመታት በየዓመቱ የእግር ጉዞ በማዘጋጀት እና ገቢ በማሰባሰብ ለካንሰር ሕሙማን እርዳታ ሲያደርግ ቆይቷል።

በኢትዮጵያ የካንሰር ሕሙማን ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የሕክምና ዕድል ሊስፋፋ ይገባል ትላለች።

ማንኛውም የካንሰር ሕመም አስቀድሞ ከታወቀ የመዳን ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑንም ትናገራለች።

አልፋ ብሬስት ካንሰር ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር በሀገሪቱ የካንሰር ሕክምና ከሚሰጡ ጥቂት ተቋማት አንዱ ለሆነው የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የማሞግራፊ ማሽን በዕርዳታ ማበርከቱን የድርጅቱ መሥራች ቬሮኒካ ሙሴ ገልጻለች።

 

ጥቂት መረጃ ስለጡት ካንሰር

·         በሀገራችንም፣ በዓለም ዙሪያም ለበርካታ ሴቶች ሞት ምክንያት ከሆኑ የካንሰር ዓይነቶች ይመደባል

·         99 በመቶ ሴቶችን የሚያጠቃ የካንሰር ዓይነት መሆኑን ጥናቶች ያመላክታሉ 

·         ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሆነ ሴቶች ለጡት ካንሰር የመጋለጥ ዕድላቸው አነስተኛ ነው

·         ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ የሆነ ሴቶች ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ በመሆኑ በየዓመቱ አሊያም በየሁለት ዓመቱ ምርመራ እንዲያደርጉ ይመከራሉ  

·         የካንሰር ታማሚ የመዳን ዕድሉ የሚወሰነው ፈጥኖ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄዱ አሊያም በመዘግየቱ ነው

 

የጡት ካንሰር ተጋላጭነትን የሚጨምሩ ምክንያቶች

·         አልኮል የሚጠጡ፣ ሲጋራ የሚያጤሱ ሴቶች የጡት ካንሰር ተጋላጭነታቸው ከፍ ያለ ነው

·         ከቅርብ ቤተሰብ መካከል የጡት ካንሰር ታማሚ ካለም ተጋላጭነት ከፍ ይላል

·         በዕድሜ መግፋት መውለድ ተስኗቸው ሆርሞን የሚወስዱ ሴቶች የጡት ካንሰር ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ በመሆኑ የቅርብ የሕክምና ክትትል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል

·         ምንም ዓይነት የጡት ካንሰር ምልክት ሳያዩ ለሌላ ምርመራ ሆስፒታል በሄዱበት ሕመሙ እንዳለባቸው የሚያውቁ ብዙዎች ናቸው።

 

የጡት ካንሰር መኖሩን የሚጠቁሙ ምልክቶች

·         ከጡት ጋር በተያያዘ ጡት ውስጥ ወይም ብብት ስር ትንንሽ እብጠቶች መከሰት

·         የጡት ቆዳ ላይ የመሰርጎድ እና የመጎተት ምልክት ማሳየት

·         ቀደም ሲል ያልነበረ የጡት ጫፍ ወደ ውስጥ የመገልበጥ ሁኔታ

·         የጡት ቆዳ መወፈር (እንደ ብርቱካን ልጣጭ ዓይነት ጠቃጠቆ ምልክት ማሳየት)

·         ከጡት ጫፍ የሚወጣ ደም የቀላቀለ ሽታ ያለው ፈሳሽ እና መሰል ምልክቶች ሲታዩ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ምርመራ ማድረግ ይገባል

 

የጡት ካንሰር ምርመራ እና ሕክምና

·         የጡት ካንሰር እንደማንኛውም ሕመም ሕክምና ያለው በሽታ ነው

·         በተለይም ሕመሙ አስቀድሞ ከታወቀ የመዳን ዕድሉ ከፍተኛ ነው

·         በተለይ ዕድሜያቸው ከ50 ዓመት በላይ ለሆነ ሴቶች የሚመከረው የጡት ካንሰር ምርመራ ዓይነት ማሞግራፊ የተሰኘው ነው

·         ሴቶች በራሳቸው ምርመራ በማድረግ የጡታቸውን የጤንነት ሁኔታ ማወቅ እንደሚችሉ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ያመለክታል

·         ይህም የጡትን የጤንነት ሁኔታ በየጊዜው በመከታተል ለውጥ ሲኖር በቶሎ ወደ ሕክምና ተቋም ለመሔድ ይረዳል

 

በንፍታሌም እንግዳወርቅ

 

#ebcdotstream #ethiopia #breastcancer #alphabreastcancer