Search

ኢትዮጵያ በቻይና ዓለም አቀፍ የአስመጪና ላኪዎች ኤክስፖ ላይ እየተሳተፈች ነው

ረቡዕ ጥቅምት 26, 2018 28

ኢትዮጵያ በስምንተኛው የቻይና ዓለም አቀፍ የአስመጪ እና ላኪዎች ኤክስፖ ላይ እየተሳተፈች ትገኛለች።

በዚሁ ኤክስፖ ላይ ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተውጣጡ የቡና፣ የቅባት እህሎች፣ ጥራጥሬ እና ሀገር በቀል ምርቶች አስመጭና ላኪዎች ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን በመያዝ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ እያስተዋወቁ ይገኛሉ።

በኤክስፖው ላይ የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ ለማስተዋወቅ የማሳያ ቦታ በባለቤትነት በመረከብ ሃገር በቀል ምርትና አገልግሎቶች እንዲያቀርቡና የሀገራችን አስመጭና ላኪዎች በቀላሉ ከዓለም አቀፉ የንግድ ማህበረሰብ ጋር እንዲገናኙ በቻይና የኢፌዴሪ ኤምባሲ እያስተባበረ እንደሚገኝ ተመላክቷል፡፡

ኤምባሲው ከኤክስፖው ጎን ለጎን በተዘጋጁ በርካታ ሁነቶች ላይም በመሳተፍ በሀገራችን ያለውን የኢንቨስትመንትና የንግድ ዕድሎችን ለዓለም አቀፉ የንግድ ማህበረሰብ እያስተዋወቀ ይገኛል።

በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው በኤክስፖ መክፈቻ ላይ በመገኘት ከቻይናና ከተለያየ የዓለማችን ክፍሎች ከተገኙ አስመጭና ላኪ ድርጅቶች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

አምባሳደሩ በዚሁ ወቅት፤ ኤክስፖው የሀገራችንን የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለማስተዋወቅ፣ ለወጪ ምርቶች ተጨማሪ ገበያ ለማስገኘት እንዲሁም በቻይና የሚላኩ ምርቶችን መጠን ለማሳደግ አይነተኛ መድረክ ነው ብለዋል።

ስምንተኛው የቻይና አለም አቀፍ አስመጭና ላኪዎች ንግድ ኤክስፖ የተከፈተው በሻንጋይ ከተማ ሲሆን የበርካታ ሀገራት መሪዎች፣ ዲፕሎማቶች፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ታድመዋል።

በኤክስፖው ላይ ከ150 በላይ ሀገራት የተውጣጡ ከ4 ሺህ በላይ አቅራቢዎች እንደሚሳተፉ ተነግሯል፡፡

ለስድስት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ኤክስፖ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎም ይጠበቃል።

በነፃነት ክንፈ

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #China #CIIE #Trade #Expo