Search

ዞህራን ማምዳኒ - በአፍሪካ የተወለደው የመጀመሪያው የኒው ዮርክ ከንቲባ

ረቡዕ ጥቅምት 26, 2018 32

በኡጋንዳ ካምፓላ የተወለደው የ34 ዓመቱ ዞህራን ማምዳኒ፣ የአሜሪካ ትልቋ ከተማ የሆነችውን ኒው ዮርክ በከንቲባነት ለመምራት ምርጫውን አሸንፎ መመረጡ ዓለምን እያነጋገረ ይገኛል።

የዘር ሐረጉ ደቡብ እስያዊ የሆነው እና ራሱን ‘የለውጥ ሐዋሪያ ነኝ’ የሚለው ዞህራን ማምዳኒ፣ በምርጫው 50.3 በመቶ ድምፅ በማግኘት ነው ተፎካካሪውን አንድሪው ኩሞን ማሸነፍ የቻለው።

የዞህራን ተፎካካሪ አንድሪው ኩሞ ደግሞ 41.6 ከመቶ ድምፅ ማግኘታቸውን ቢቢሲ በዘገባው አመላክቷል።

ከጥቂት ወራት በፊት በኒው ዮርክ ምክር ቤት ብዙም እውቅና ያልነበረው ተመራጩ ከንቲባ ዞህራን፤ በምረጡኝ ቅስቀሳው የከተማዋን ነዋሪዎች ቀልብ የሚገዙ ንግግሮችን በማድረግ እውቅና ማግኘት ችሏል።

"ከየትኛውም ቦታ እንመጣለን፤ ነገር ግን አብረን እንገነባለን" በሚለው ንግግሩም የበርካቶችን ቀልብ ገዝቷል።

ዴሞክራቲክ ሶሻሊስት እንደሆነ የሚናገረው ዞህራን፣ በኒው ዮርክ የቤት ኪራይ እንዳይጨምር እግድ መጣል፣ በማኅበራዊ የቤት ልማት ተመጣጣኝ ቤትን መገንባት፣ ጤናማ የሸቀጥ ፍጆታዎችን በአነስተኛ ዋጋ ማቅረብ፣ ነፃ የልጆች እንክብካቤ፣ ሁሉም የአውቶብስ የትራንስፖርት አገልግሎት ነፃ እንዲሆን በሚሉ እና ሌሎች ሐሳቦች ላይ አተኩሮ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረጉን አልጀዚራ ዘግቧል።

ግራ ዘመም ፖለቲከኛ፣ የስደተኛ ልጅ እንዲሁም የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነው ዞህራን የበርካታ ዓመታት ልምድ ያላቸውን አንድሪው ኩሞን ያሸንፋል ተብሎ አልተጠበቀም ነበር።

አንድሪው ኩሞ በምርጫው መሸነፋቸውን አምነው፣ የእንኳን ደስ ያለህ መልዕክት ለተፎካካሪያቸው ዞህራን አስተላልፈዋል።

በንግግራቸውም "ኒው ዮርክ ትልቅ ከተማ ነች፤ ከተማችንን እንወዳታለን፤ በአንድነት አብረን ለነዋሪዎች እንሠራለን" ሲሉም ተደምጠዋል።

ዞህራን ምርጫውን ካሸነፈ በኋላ ባደረገው ንግግር አትዮጵያውያንን፣ የመናውያንን፣ ሴኔጋላውያን፣ ኡዝቤክስታናውያንን ጨምሮ ድጋፍ የሰጡትን በመዘርዘር አመስግኗል።

በመሐመድ ፊጣሞ

#EBC #ebcdotstream #USA #NewYork