የሴራሊዮን መንግሥት እና የዓለም አቀፉ የታዳሽ ኢነርጂ ኤጀንሲ በጋራ ያዘጋጁት ሁለተኛው የአፍሪካ ታዳሽ ኃይል የኢንቨስትመንት እና የአጋርነት ፎረም በሴራሊዮን ፍሪታውን ተካሂዷል።
“የአፍሪካ ኢነርጂ ሽግግር እና አረንጓዴ ኢንዱስትሪ ለማፋጠን ኢንቨስትመንትን ማሳደግ” በሚል መሪ ሐሳብ በተካሄደው ፎረሙ ላይ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ አመራሮች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የኢነርጂ ዘርፍ መሪዎች እና የልማት አጋሮች ተሳትፈዋል።
ሁነቱ በአፍሪካ የታዳሽ ኢነርጂ ኢንቨስመንት ማሳደግ እና አረንጓዴ መር ኢንዱስትሪን ማስፋት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የመከረ ሲሆን ኢትዮጵያም በኢንቨስትመንት ፎረሙ ላይ ተሳትፎ አድርጋለች።
የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የታዳሽ ኃይል አማካሪ ተመስገን ተፈራ የኢንቨስትመንት ፎረሙ በአፍሪካ የታዳሽ ኢነርጂ ሽግግርን እውን ማድረግ የሚያስችል ሀብት ለማሰባሰብ፣ የቴክኒክ ድጋፍ ለማድረግ እና የግሉን ዘርፍ ድጋፍ ለማሳደግ ቁልፍ ሚና የሚወጣ መድረክ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ሽግግርን እውን ለማድረግ እና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ እንደሆነችም ተናግረዋል።
ሁለተኛ የአፍሪካ ታዳሽ ኃይል የኢንቨስትመንት እና የአጋርነት ፎረም እ.አ.አ በ2024 በኬንያ ናይሮቢ የተካሄደው የመጀመሪያ ፎረም ውጤቶችን ገምግሟል።
በናይሮቢ የተካሄደው ፎረም በተሳታፊ ሀገራት ለተለዩ የአንድ ጊጋ ዋት ገደማ የታዳሽ ኢነርጂ ፕሮጀክቶች መንግሥታት፣ የፋይናንስ ተቋማት እና ባለሀብቶች የ2.7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሀብት ለመስጠት ቃል መግባታቸው የሚታወስ ነው።
እንደ ኢዜአ ዘገባ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ የፎረሙ ተሳታፊ የአፍሪካ ሀገራት በአፍሪካ የታዳሽ ኢነርጂ አቅም እና ሀብቱን ጥቅም ላይ በማዋል መካከል ያለውን ልዩነት ለመሙላት ፋይናንስ ፈሰስ ለማድረግ እና ፕሮጀክቶችን ለመተግበር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን መግለጻቸውን የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል።
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #Africa #renewableenergy