Search

የዘመኑ የአርበኝነት መገለጫ ድህነትን ታሪክ ማድረግ ነው - ምሁራን

ረቡዕ ጥቅምት 26, 2018 49

የዘመኑ ትውልድ የአርበኝነት መገለጫ የሀገር ፍቅርና ድህነትን ታሪክ ማድረግ ነው ሲሉ ምሁራን ገለጹ፡፡

የፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግኑኝነት ምሁር የሆኑት አቶ እንዳለ ንጉሤ ከኢቲቪ አዲስ ቀን መሰናዶ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያዊያን ለረጅም ዘመናት የአርበኝነት ገድሎችን የፈፀሙ ህዝቦች ናቸው ብለዋል፡፡

ቀደምት አባቶች እና እናቶች ከራስ በላይ ሀገር መቅደም እንዳለባት፣ ትልቅ ጽናትን፣ መተባበርን፣ በመሪ ስር መመራትን አስተምረውናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

እንደ ላሊበላና አክሱም ያሉ ድንቅ ስራዎች የኢትዮጵያውያን በፅናት የመቆም እና የመተባበር ምሳሌዎች መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡

ኢትዮጵያውያን በአንድነት በመቆም እንደ ዓድዋ ያለ የገዘፈ ታሪክ መስራት እንደሚቻልም አሳይተዋል ነው ያሉት፡፡

ባለፉት 50 ዓመታት በሀገሪቱ የታዩ የእርስ በእርስ ግጭቶች ሀገሪቱ ያሏትን ሀብቶች እንዳትጠቀም እንዳደረጋትም አስታውሰዋል፡፡

የውጭ ጠላቶችም ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በማበር የሀገሪቱ እድገት እንዳይፋጠን አድርገዋል ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡

የዘመኑ ትውልድ የአርበኝነት መገለጫዎች በርካታ እንደሆኑ ያነሱት አቶ እንዳለ፤ ህዝብን በቀናነት ማገልገል እና ከድኅነት ለመውጣት የሚደረገው ጥረት የዚህ እሳቤ ዋነኛ መገለጫዎች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡

የታሪክ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት አቶ በለጠ ሲጌቦ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአርበኝነቷ ከሌሎች ሀገራት ልዩ ያደርጋታል ያሉ ሲሆን፤ ኢትዮጵያዊያን የተሳሰረ እና የተጋመደ ታሪክ እና ማንነት ያለን ህዝቦች ነን ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የ21ኛ ክፍለ ዘመን የአርበኝነት መገለጫ የሀገር ፍቅር እና ድህነትን ታሪክ ማድረግ ላይ ነው ብለዋል፡፡

ዘመኑን እና ወቅቱን የጠበቀ እውቀት የተላበሰ ትውልድ የሚያስፈልግበት ጊዜ እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡

የቀደሙ አያቶቻችን በዱር በገደሉ ተዋድቀው መስዋት የከፈሉላትን ሀገር የዘመኑ ወጣት በመደመር የሀገር እድገት እና ልዕልና ላይ ሊሰራ ይገባል ሲሉ አመላክተዋል፡፡

በሜሮን ንብረት

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #patriotism