Search

ለበርካታ ሀገራት አዲስ የአብሮነት ምዕራፍ የከፈተው ሀገራዊ ምክክር

ማክሰኞ ጥቅምት 25, 2018 348

ሀገራዊ ምክክር ጥልቅ የፖለቲካ ቀውሶችን ለመፍታት እና ለአካታች ፖለቲካዊ ሽግግሮች መንገድ ለመክፈት ሁሉን ያካተተ፣ ሰፊ እና አሳታፊ ኦፊሴላዊ ውይይት ነው።

ተፋላሚ ፓርቲዎችን፣ የፖለቲካ መሪዎችን፣ የሲቪል ማኅበረሰብን እና ሌሎች ቁልፍ ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ ለሀገር የጋራ የፖለቲካ ራዕይ እና ፍኖተ ካርታ እንቅፋት የሆኑ ቁርሾዎችን ይለያል።

እንደ የሀብት ክፍፍል፣ ሕገ-መንግሥታዊ መዋቅር እና የብሔር ክፍፍል ያሉት አወቃቀሮች ትተው ያለፉት ቁርሾዎች የተፈጠሩባቸውን ምክንያቶች በመለየት ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ምክክር እጅጉን ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ይገለጻል።

በውይይቱ ሂደት ሁሉም ቅሬታውን ፊትለፊት በማቅረብ የሰላም እና የሽግግር ስምምነት በመፍጠር የሕዝብ ድጋፍን መሠረት ያደረገ ሁሉን አካታች የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር መሠረት ይጥላል።

ምክክር ብዙውን ጊዜ ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያዎች ወይም አዲስ ቋሚ ሕገ-መንግሥት እንዲዘጋጅ የበርካታ ሕዝብ ድምፅ የሚሰማበት ሲሆን፣ ስምምነት የተደረሱባቸውን ማሻሻያዎችን ተቋማዊ ማድረግ የሚያስችል ነው።

የጋራ ስምምነት ያልተደረሰባቸው ጉዳዮች ደግሞ ለሕዝበ ውሳኔ ቀርበው አብላጫ ድምፅ የሚያገኙት የማሻሻዎቹ አካል ይሆናሉ።

በርካታ ሀገራት በዚህ ሂደት ችግሮቻቸውን ፈትተው ወደ ሰላማዊ፣ የተረጋጋ እና የተዋሃደ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ተመልሰዋል።

በዚሁ መንገድ ችግሮቻቸውን ፈትተው ጠንካራ ሀገረ መንግሥት መገንባት የቻሉትን ሀገራት ተሞክሮ እንመልከት፦

ደቡብ አፍሪካ

1948 እስከ 1994 በሀገሪቱ ሰፍኖ የቆየው የአፓርታይድ ሥርዓት በከፋው የዘረኝነት አገዛዙ ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያን ላይ ከፍተኛ ስቃይ ያደረሰ ነበር።

ስቃዩ የመረራቸው ጥቁሮችም የመብት ትግል እንቅስቃሴ ሲጀምሩ በርካቶች ለእስራት፣ ለስደት እና ለሞት ተዳርገዋል። ከመብት ታጋዮች መካከል የነበሩት ኔልሰን ማንዴላ እና ጓዶቻቸውም 27 ዓመታት የፅኑ እስራት ሰለባ ሆነዋል።

ነገሩ እየከረረ መምጣቱ ሀገሪቱን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንደሚያመራት የተረዱት ፕሬዚዳንት ፍሬድሪክ ክለርክ እነ ኔልሰን ማንዴላን ከእስር ቤት ፈትተው የይቅርታ እና እርቅን ጎዳና ጀመሩ።

የእውነት አፈላላጊ እና እርቅ ኮሚሽን (Truth and Reconciliation Commission) በማቋቋም ቁርሾ የፈጠሩ ወንጀሎችን በመለየት ወደ ይፋዊ ይቅርታ እና ምሕረት የሚያመሩ መንገዶችንም አመቻቹ።

የምክክር ሂደቱ በተሃድሶ ፍትሕ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ያለፈውን በይቅርታ ለማለፍ ለጎጂዎች ስቃይ በይፋ እውቅና መስጠት ላይ ትኩረት ያደረገ ነበረ። ይህም ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገውን ሽግግር አመቻችቶ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ኔልሰን ማንዴላን የመጀመሪያው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት አድርጓል።

የፍትሕ ሂደቱ ሥርዓታዊ ጭቆና በፈጠሩት ነጮች ላይ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን በትግል ሂደት በደል የፈጸሙ ጥቁሮችንም ያካተተ በመሆኑ ውጤቱም የተሟላ ሰላምን ሊያመጣ ችሏል።

ሩዋንዳ

ሩዋንዳ 1994 በሁቱ እና ቱትሲዎች መካከል በተፈጠረ ግጭት በመቶ ቀናት ብቻ 800 ሺህ በላይ ዜጎቿን የፈጀ እልቂት የተካሄደባት ሀገር ነች። ሀገሪቱ ዛሬ ያንን ክፉ ጠባሳ ረስታ ከአፍሪካ አዳጊ ኢኮኖሚዎች መካከል አንዱን የገነባቸው ችግሮቿ ላይ ተወያይታ ዘላቂ መፍትሔ በመውሰዷ ነው።

ያንን ችግር እንድትፈታ ያስቻላትን ሂደት የመራው ደግሞ የብሔራዊ አንድነት እና እርቅ ኮሚሽን (National Unity and Reconciliation Commition /NURC/) ነበር።

ኮሚሽኑ በቱትሲዎች ላይ የተፈፀመውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በመለየት ፍትሕን፣ እውነትን፣ ሰላምን እና ደኅንነትን ለማምጣት ያለመ ሁለገብ ጥረት አካል ሲሆን፣ የመጨረሻ ግቡም ቅራኔዎች ተፈትተው ብሔራዊ አንድነት በመገንባት የሚያስችል ምክረ ሐሳብ ማቅረብ ነው።

ኮሚሽኑ ርዋንዳ በእርቅ እና በሽግግር ፍትሕ አማካኝነት የሚጨበጥ ለውጥ እንድታመጣ ያስቻለ ነው። በሂደቱ በተለየው መሠረት የዘር ማጥፋት ተዋናዮችን ወደ ሕግ በማቅረብ በጥፋተኞች ላይ ሕጋዊ እርምጃዎች ተወስደው ፍትሕ እንዲሰፍን ተደርጓል።

ዋና ዓላማው የሆነውን የተዋሃደ ብሔራዊ ማንነትን መልሶ በመገንባት፣ ሀገሪቱን በማረጋጋት እና የፍትሕ መዛግብትን በማፅዳት ስኬታማ ሆኗል።

ካናዳ

ካናዳ ነባር የሀገሬውን ተወላጆች ሕፃናት ከቤተሰቦቻቸው በግዳጅ በመውሰድ ወደ ኢንዲያን አዳሪ ትምህርት ቤት በማስገባት ለረጅም ጊዜ ስታስተምር ቆይታለች።

ኢንዲያን አዳሪ ትምህርት ቤት በካናዳ መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግ ሲሆን፣ በካቶሊክ፣ የካናዳ ኢንግሊካን፣ የካናዳ ዩናይትድ እና በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጥምረት የሚተዳደር ነበር።

ዓላማው ልጆችን ከቤተሰቦቻቸው እና ከባህላቸው ተፅዕኖ ማውጣት እና "ዋና" ከተባለው የካናዳ ባህል ጋር ማዋሃድ ነበር። በግምት 30 በመቶ የሚሆኑት የሀገሬው ተወላጅ ልጆች በዚህ ሥርዓት እንዲማሩ ተደርጓል። ይህ 1879 እስከ 1997 (..) የቆየ ሥርዓት የነባር ሕዝቦችን ባህል ውድመት ያስከተለ በደል በመፈፀም ታሪካዊ የትውልዶች ስብራት ፈጥሯል ተብሎ ታመነበት።

ይህ አካሄድ የነባር ሕዝቦችን ታሪክ ከማጥፋቱም ባለፈ በትምህርት ቤቱ ውስጥ ሲማሩ በነበሩ ተማሪዎች ላይ ያደረሰው ሥነ-ልቦናዊ እና አካላዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑን የካናዳ መንግሥት አምኖ ተቀበለ።

2008 የካናዳ መንግሥትን በመወከል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይፋዊ ይቅርታ የጠየቁ ሲሆን፣ ይህም ቀጣይነት ያለው የእርቅ ጉዞ መጀመሩን አመልክቷል። ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት የካናዳ እውነት እና እርቅ ኮሚሽን (Truth and Reconciliation Commission) ተቋቋመ።

ኮሚሽኑ የተቋቋመው በአዳሪ ትምህርት ቤቱ ሥርዓት የደረሱ የባህል፣ ታሪክ እና የሥነ-ልቦና ተፅዕኖዎች ለመመዝገብ እና ብሔራዊ የእርቅ ሂደትን ለመምራት ነው። በትምህርት ቤቱ ተማሪ ከነበሩ እና በሕይወት ከተገኙ ሰዎች፣ ከቤተሰቦቻቸው እና ከሌሎችም 6 ሺህ 750 ምስክርነቶችን ሰብስቧል።

ለሥድስት ዓመታት ምስክርነቶቹን ሲያሰባሰብ የቆየው ኮሚሽኑ .. 2015 በልዩ ሁኔታ ሊታዩ የሚገባቸውን 94 ጉዳዮችን ለይቶ ለውሳኔ አቅርቧል።

ከሁሉም ተለይቶ እንዲታይ የተደረገው ጉዳይ በትምህርት ቤቱ የተፈጸመው ማንነትን ማጥፈት (cultural genocide) ነበረ። ሕፃናትን በግድ ከቤተሰቦቻቸው ለይቶ መውሰድ፣ ቋንቋቸውን እንዳይጠቀሙ ማድረግ፣ ወሲባዊ እና አካላዊ ጥቃት ማድረስ እንዲሁም በቂ ምግብ እና ሕክምና በማጣት በርካቶች ለሞት መዳረጋቸው ኮሚሽኑ የደረሰበት ውጤት ነው።

በመጨረሻም ከሚሽኑ ለእርቅ እና ይቅርታ ሂደቱ አስፈላጊ የሆኑ ምክረ ሀሳቦችን አቅርቧል። እነዚህን የእርቅ እና ይቅርታ ሂደቶችን የሚያመቻች ብሔራዊ የእውነትና እርቅ ማዕከል (National Centre for Truth and Reconciliation /NCTR/) ተቋቁሟል። በዚህም ይቅርታ፣ የሥነ-ልቦና ግንባታ፣ የገንዘብ ካሣ፣ ሕክምና እና ሌሎች እርምጃዎች ተወስዶ ጉዳዩ በእርቅ እና ይቅርታ ተቋጭቷል።

ሰሜን አየርላንድ

ሰሜን አየርላንድ ለአሥርተ ዓመታት የቆየችበት አመፅ እና ግጭት ሥር የሰደዱ የፖለቲካ ስበራት፣ ማኅበራዊ ቀውስ እና ክፍፍሎችን የፈጠሩባት ሀገር ነበረች። የግጭቱ ምሕዋሮች ደግሞዩኒየኒስቶችእናናሽናልስቶችነበሩ።

ዩኒየኒስቶቹሀገራቸው የዩናይትድ ኪንገደም አካል ሆና እንድትቀጥል የሚፈልጉ ነበሩ።ናሽናሊስቶችሰሜን አየርላንድ ራሷን የቻለች ሀገር መሆን አለባት የሚል አቋም ያራምዱ ነበር። ይህም በሁለቱ ቡድኖች መካከል ማባሪያ የሌለው ግጭት ፈጠረ።

ናሽናልሽቶቹ ኅዳጣን (minority) በመሆናቸው ሥርዓታዊ መድልኦ እየተደረገባቸው ዝም ለማስባል ጥረት ቢደረግም ጉዳዩ ግን መንግሥት በቀላሉ የሚቆጣጠረው ሳይሆን ቀርቶ ወደ ተደጋጋሚ ግጭት እና ሰላም ማጣት በማምራት ሀገሪቱን እረፍት ነፃት።

ነገሩ ስር እየሰደደ ሄዶ ወደ ትጥቅ ግጭት እያመራ ለሀሪቱ ኅልውና ስጋት ሲሆንም የእርቅ እና ይቅርታ ሂደት እንዲጀመር ተወሰነ።

ዋናው የእርቅ እና የሰላም ሂደት .. ሚያዝያ 10 ቀን 1998 በተፈረመው የቤልፋስት የስቅለቷ ዓርብ ስምምነት (Good Friday Agreement (GFA)) ተጠናቀቀ። 

የእርቅ ሂደቱ በዋነኛነት ተቋማዊ የሰላም ግንባታ መንገድን የተከተለ ነበር። ይህም በተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሥልጣን መጋራትን፣ የፖሊሲ ማሻሻያ እና በማኅበረሰብ በሚመራ ውይይት መተማመንን ለመገንባት እና አብሮነትን ማጠናከር የሚያስችሉ ተግባራትን ያካትታል። ይህ ሂደት ከሌሎቹ የሚለየው በካሣ እና ሽግግር ፍትሕ ላይ ሳይሆን በውይይት እና በተቋማዊ ማሻሻያ ላይ አፅንኦት ሰጥቶ መጠናቀቁ ነው።

የሀገራዊ ምክክሩ ተስፋ በኢትዮጵያ

ኢትዮጵያ በሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደት የተፈጠሩ ቁርሾዎች ተለይተው ለምክክር እንዲቀርቡ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ ሥራውን እየሠራ ይገኛል።

ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እየሠራ ያለው አካታች የሆነ ውሳኔ ሰጪነትን ለማረጋገጥ፣ የዜጎችን ጥያቄዎች ለመረዳት፣ ድምፃቸው ያልተሰማ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ለማስተናገድ፣ ዜጋ-ተኮር መፍትሔዎችን ለማመንጨት እና መተማመንን እና ማኅበራዊ ትሥሥርን ለመገንባት እና ለማደስ ነው።

በሂደቱም ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች በአካል እና በተለያዩ የመልዕክት ማስተላለፊያ መንገዶች ሐሳባቸውን እንዲሰጡ ሁኔታዎች ተመቻችተዋል።

በዚህም ኮሚሽኑ እስከ አሁን 11 ክልሎች እና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች (አዲስ አበባ እና ድሬደዋ) ስኬታማ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የተሳታፊ ልየታ ተግባራት ማከናወን ችሏል።

በተጨማሪም በሰሜን አሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ ከሚኖሩ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት ጋር የገጽ ለገጽ እና የበይነመረብ (ቨርቹዋል) ውይይት በማድረግ አጀንዳ የማሰባሰብ እና የተሳታፊ ልየታን አካሂዷል።

ኮሚሽኑ በቀጣይ እነዚህ የተለዩ ዋና ዋና አጀንዳዎች ተቀምረው ብሔራዊ የምክክር መድረክ ለማዘጋጀት እየሠራ ይገኛል።

በለሚ ታደሰ