ቀጣዩ የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ የሚካሄደው ከ12 ወራት በኋላ ቢሆንም በፕሬዚዳንት ትራምፕ የተበሳጩት ዴሞክራቶች ከአሁኑ ጠንካራ እንቅስቃሴ ጀምረዋል፡፡
አንዳንድ ግዛቶችም ዋናው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳርፉ የሚችሉ የግዛት አስተዳዳሪዎች እና ምክር ቤት ምርጫ አድርገው ውጤታቸው ይፋ እየሆነ ነው፡፡
አሁን እየተደረገ ባለው አንቅስቃሴ ሴኔቱን ተቆጣጥረው ያሉት ሪፐብሊካኖች በምርጫው 28 ወንበሮችን ሊያጡ እንደሚችሉ የለንደን ኢኮኖሚክስ እና ፖለቲካል ሳይንስ ጥናት ያመላክታል፡፡
በኒውዮርክ ከተማ ከንቲባ ምርጫ እንዲሁም የኒው ጀርሲ፣ የቨርጂኒያ እና የካሊፎርኒያ ገዥዎች ምርጫን ዴሞክራቶች ማሸነፋቸው የአጋማሽ ዘመን ምርጫው ለሪፐብሊካን እንደሚከብድ ማሳያ መሆኑን የሲ.ቢ.ኤስ መረጃ አመልክቷል።
በኒው ጄርሲ እና ቨርጂኒያም ዴሞክራቶች በሰፊ ነጥብ እየመሩ ሲሆን፣ የሌሎች ግዛቶች ውጤትም ተመሳሳይ ሊሆን እንደሚችል ነው ሲ.ቢ.ኤስ ያመለከተው፡፡
በተለይም የሪፐብሊካን ደጋፊዎች ይበዙባታል ተብሎ በሚታሰብባት ኒው ዮርክ የከንቲባ ምርጫ ውጤት አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ የከተማዋ ከንቲባ ሆነው የተመረጡት ኡጋንዳ ካምፓላ የተወለዱት የ34 ዓመቱ የዴሞክራት ፓርቲ አባል ዞህራን ማምዳኒ ናቸው፡፡ ዞህራን ምርጫውን ማሸነፋቸውን ተከትሎ ባደረጉት ንግግር "ዛሬ የተሸነፈው ትናንሽ ሀሳብ የያዘው ትልቅ ገንዘብ ነው" ብለዋል፡፡
ለደጋፊዎቻቸውም፣ "ለውጥ እና አዲስ የፖለቲካ አካሄድ እንደሚያስፈልግ ወስናችኋል፤ ሁላችንንም የምትመስል ከተማ እንዲኖረን ኃላፊነት ሰጥታችሁኛል" በማለት ደስታቸውን ገልጸዋል።
የአሜሪካ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ በሀገሪቱ ከሚካሄደው አጠቃላይ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሁለት ዓመት በኋላ የሚካሄድ ነው።
ምርጫው በሥልጣን ላይ ባለው ፕሬዝዳንት እና ነጩን ቤተ መንግሥት በሚቆጣጠረው ፓርቲ ላይ እንደሚሰጥ ሕዝበ-ውሳኔ የሚቆጠር ነው።
በኮንግረስ እና በግዛት መንግሥታት መካከል ያለውን የኃይል ሚዛን የሚወስን፣ የቀሩትን ሁለት ዓመታት የፕሬዚዳንቱን አጀንዳ በቀጥታ የሚነካ እና ለቀጣዩ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት እንደ ሕዝበ ውሳኔ በመሆኑ በልዩ ሁኔታ ይጠበቃል።
የአሜሪካ የህዝብ የተወካዮች ምክር ቤት 435 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፣ እነዚህን መቀመጫዎች የሚይዙት ተወካዮች በየሁለት ዓመቱ ይመረጣሉ፡፡
100 መቀመጫዎች ካሉት ሴኔት ውስጥ አንድ ሦስተኛ በሚሆኑት ላይም ምርጫ ይደረጋል፡፡ በሴኔቱ አብላጫውን ወንበር የሚይዘው ፓርቲ የፕሬዚዳንቱን ካቢኔ እጩዎች፣ አምባሳደሮች፣ የፌደራል ዳኞች እና የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችን ሹመት፣ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ለማጽደቅ ሥልጣን ስለሚያገኝ ሴኔቱን ለመቆጣጠር የሚደረገው ፉክክር ከፍተኛ ነው።
ከ30 በላይ ግዛቶች በዚሁ የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ገዥዎቻቸውን እና ሕግ አውጪዎችን፣ ዳኞችን እና የአካባቢ ባለሥልጣናትን ይመርጣሉ።
በ36 ግዛቶች እና 3 አካባቢዎች ያሉ አስተዳደሮችን መቆጣጠር የአጠቃላዩን ምርጫ ውጤት የሚወስን መሆኑ ይጠቀሳል፡፡
የግዛቶቹ አስተዳዳሪዎች እንደ አየር ንብረት ለውጥ፣ ፅንስ ማቋረጥ እና የምርጫ አስተዳደር ፖሊሲዎችን የመወሰን አቅም ስለሚኖራቸው ከእነዚህም አብላጫውን ለመያዝ ያለው ፍትጊያም ከባድ ነው።
የፕሬዚዳንቱ ፓርቲ ምርጫውን የሚያሸንፍ ከሆነ ፕሬዚዳንቱ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚሰጡትን ውሳኔ የሚያቀልላቸው ሲሆን፣ ውጤቱ በተቃራኒ ከሆነ ደግሞ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አፈጻጸምን ጨምሮ በተለያዩ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ምክር ቤቶቹን የተቆጣጠረው ፓርቲ ተፅዕኖ ከፍተኛ (Gridlock) ይሆናል፡፡
ምርጫው በ‘ጄኔሬቲቭ’ ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና ሌሎች የቴክኖሎጂ ውጤቶች በሚፈበረኩ ሀሰተኛ መረጃዎች ተፅዕኖ ስር ሊወድቅ እንደሚችል መፈራቱ አሳሳቢ ጉዳይ ሆኗል።
በለሚ ታደሰ
#EBC #ebcdotstream #USA #Midterm_election