የጊቤ መንግሥታት ከ16ኛው እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን በኢትዮጵያ ደቡብ ምዕራብ ክፍል ዝነኛ የነበሩ አምስት ሥርወ መንግሥታት ናቸው።
በበለፀገ ባህላቸው እና የንግድ እንቅስቃሴያቸው የሚታወቁ ሲሆን ቡና የአካባቢው ምጣኔ ሀብት መሠረት ነበር።
እነዚህ በጅማ እና አካባቢው የነበሩ አምስቱ የጊቤ መንግሥታት ጅማ፣ ሊሙ-ኢናሪያ፣ ጌራ፣ ጎማ እና ጉማ ይባሉ ነበር።
ከጊቤ ግዛቶች አንዱ የሆነው የጅማ መንግሥት ከጊቤ መንግሥታት መካከል ከፍተኛው ተፅዕኖ ፈጣሪ እና እጅግ የበለጸገ እንደነበር በታሪክ ተመዝግቧል።
የጅማ መንግሥት በጂረን (የአሁኗ ጅማ) ከትሞ የነበረ ሲሆን የተመሠረተውም በ18ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ነው።
በአባ ጅፋር መሪነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰው የጅማ ሥልጣኔ በዚያን ዘመን ለም መሬቷ እና በአካባቢው ምቹ የአየር ንብረት ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና አምርታ ወደ ውጭ እንድትልክ አስችሏታል።
በዘመኑ ጅማን ከሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች እስከ ቀይ ባሕር የሚያገናኙ የንግድ መስመሮችን በመጠቀም የዓረብ እና ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ ባለሃብቶች ጋር የንግድ ልውውጥ እስከማድረግ ተደርሷል።
ይህ የንግድ ግንኙነት ከኢትዮጵያ አልፎ እስከ መካከለኛው ምሥራቅ እና የዓረብ ሀገራት የዘለቀ ስለነበር በርካቶች ከመካከለኛው ምሥራቅ ወደ ጅማ በመምጣት በንግድ እና ሌሎች ዘርፎች ለመሰማራት ዕድሉን አግኝተዋል።
ከአንጋፋዎቹ የኢትዮጵያ ከተሞች በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀሰዋ ጅማ ለረጅም ጊዜ ተቀዛቅዛ ሥልጣኔዋን እና የሀብት ምንጭነቷን የማይመጥን ደረጃ ላይ ቆይታለች።
አሁን ግን ዳግም ትንሣኤዋ የደረሰ ይመስላል፤ ታታሪ ሕዝቦቿ ደረጃዋን በሚመጥናት መልኩ እየገነቧት ነው።
ሰላም እና ልማትን ራዕይዋ አድርጋ በኮሪደር ልማትም ሆነ በአጠቃላይ እንቅስቃሴዋ አርዓያ የሚሆን ለውጥ እያመጣች ትገኛለች።
ኅብረ ብሔራዊት የሆነችው ጅማ በማንኛውም ልዩነት ማንም የማይገፋባት እና ሁሉም ተባብሮ የሚኖርባት የሰላም ደሴት ስትሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት ሰላሟን ለማደፍረስ የሞከሩትን አሳፍራ መልሳለች።
በየአቅጣጨው ደን የሚታይባት አረንጓዴ ነች፤ በቡናዋ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ትደግፋለች፤ ማርም ሌላው የጅማ በረከት ነው፤ ከዋንዛ የሚሠሩት እና ጠቢብ እጆች ያረፉባቸው ቁሳቁቿ የትም ቢሆንም መለያዋ ናቸው።
እንደ "አዌቱ ፕሮጀክት" እና የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት እድሳት ያሉ ፕሮጀክቶች ደግሞ ጅማን ሁሉም የሚመኛት እንደትሆን አድርጓታል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ዋነኛ የንግድ ማዕከል የሆነችው ጅማ፣ በተለይ በቡና እና በቅመማ ቅመም ምርት በሀገራችን ካሉት ግንባር ቀደም አካባቢዎች አንዷ ናት፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሩዝ ምርትም ከፍተኛ ለውጥ እያመጣች ነው።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አካል የሆነው የጅማ ምርምር ማዕከል የቡና እና የቅመማ ቅመም ምርትን በማሻሻል ዘርፍ የተሰማራ ሲሆን፣ ከአካባቢውም አልፎ ለመላው ኢትዮጵያ የሚተርፍ ሥራ እየሠራ ይገኛል።
"በማኅበረሰብ ውስጥ ነን!" የሚል መሪ ቃል ያለው ጅማ ዩኒቨርሲቲ በበርካታ ማኅበረሰብ አቀፍ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚሳተፍ የማኅበረሰብ ተቋም ነው።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኢቢሲ) “ወደ ይዘት” በሚለው እንቅስቃሴው የተጨማሪ ይዘት ምንጭ ስቱዲዮ ከከፈተባቸው አካባቢዎች መካከል አንዷ ታሪካዊቷ ጅማ ናት።
ኢቢሲ በዚያ ባስገነባው ስቱዲዮው የጅማን ኅበረ ብሔራዊነት፣ መልካም እሴቶች፣ ታሪክ እና የተፈጥሮ ሀብት ከምንጩ መቅዳት ለመላው ኢትዮጵያ ያደርሳል።
በለሚ ታደሰ
#EBC #ebcdotstream #ጅማ #ኢቢሲወደይዘት