Search

ፈተናዎችን ተቋቁሞ በመገንባቱ የሁለት ወራቱን ጉዞ ወደ አስር ሰዓታት ያሳጠረው የፓናማ ካናል

እሑድ ጥቅምት 30, 2018 781

ዛሬ ላይ በዓመት እስከ 14 መርከቦችን የሚያስተላልፈው እና መርከቦች ይወስድባቸውን የነበረውን ከሁለት ወራት በላይ የሚፈጅ ጉዞ ወደ አስር ሰዓታት ማሳጠር የቻለው የፓናማ ካናል የሰው ልጅ ታላቅ የምህንድስና ስኬት ሆኖ ይወደሳል።

የአትላንቲክ እና የፓሲፊክ ውቅያኖሶችን ማገናኘት የቻለው የፓናማ ካናል በግንባታው ወቅት በሺ የሚቆጠሩ ሠራተኞች የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለውበታል።

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ከመገንባቱ በፊት ትላልቅ መርከቦች ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ወደ ፓሲፊክ አካባቢ ለመጓዝ የደቡብ አሜሪካን አህጉር መዞር ይጠበቅባቸው ነበር።

ይህም 13 ኪሎ ሜትሮችን መጓዝ የሚጠይቅ ረጅም የባሕር ላይ ጉዞ በመሆኑ ከነዳጅና ከአጠቃላይ ወጪዎች አንጻር እጅግ ውድ ሲሆን፤ የጉዞ መስመሩም አደገኛ ነበር።

ይህንን የተገነዘበው የፈረንሳይ መንግሥት ከጊዜም ሆነ ከወጪ አንፃር አስቸጋሪ ለሆነው የጉዞ መስመር መፍትሄ ለመስጠትና አጭር መተላለፊያ ለመፍጠር በማቀድ ግዙፍ የማስተላለፊያ ካናል ለመገንባት አቀደ።

የፈረንሳይ መንግሥት ይህን የካናል ግንባታ እውን ለማድረግ ወደሥራ ሲገባ የስዊዝ ካናልን በመገንባት ዝናን ያተረፉትን ፈረንሳዊው ዲፕሎማት ፈርዲናንድ ለሴፕስን የፕሮጀክቱ የበላይ ተቆጣጣሪ አድርጎ በመሾም ነበር ሥራውን የጀመረው።

ለወራት ከፈጀ ጥናት በኋላም የስዊዝ ካናልን የግንባታ ዲዛይን እውን በማድረግ በሺህ የሚቆጠሩ ሰራተኞችና በጊዜው ዘመናዊ የሚባሉ የኮንስትራክሽን መሳሪያዎች ወደ ስፍራው ተጓጉዘው እ.አ.አ. 1881 ሥራው እንደተጀመረ  በአካባቢው በነበሩ የቢጫ ወባና ሌሎች በሽታዎች የተነሳ የበርካታ ሠራተኞች ሕይወት ማለፍ ጀመረ።

በዚህ ምክንያትም 20 በላይ ሠራተኞች ለሕልፈት ተዳርገዋል።

በዚህ አይነት መልኩ የተለያዩ በሽታዎችን በመጋፈጥ ሥራው ቢቀጥልም በመሐል ያልታሰበ የምህንድስና ስህተት መፈጠሩ ታወቀ።

በዚህም በካናሉ መሐል ከሚገኘው የመሬት ከፍታ ጋር ያልተጣጣመው የምህንድስና ሥራ እና የቦታው አስቸጋሪነት የመጀመሪያው የግንባታው ፈተና ሆነ። ቦታው የመሬት ናዳ ያለበት በመሆኑም በየጊዜው ሠራተኞች ላይ አደጋ ይደርስ ነበር።

ሌላኛው ፈተና ሆኖ የተገኘው ደግሞ የፈረንሳይ ኢኮኖሚ የተዳከመበት ወቅት በመሆኑ ስህተቱን አርሞ ፕሮጀክቱን ለመሥራት የማይቻልበት የገንዘብ እጥረት አጋጠመ።

በየጊዜው ሠራተኞች ላይ የደረሰው ሕልፈት የግንባታው ዲዛይን ስህተት እና የፋይናንስ እጥረት ተደማምረው ፈረንሳይ 13 ዓመታት ግንባታ ሒደት በኋላ ፕሮጀክቱን እንድትተወው ተገደደች።

በእነዚህ ተግዳሮቶች ምክንያት ሥራው ተጀምሮ የተወሰነ ደረጃ የደረሰው የፓናማ ካናል 10 ዓመታት ግንባታው ከተቋረጠ በኋላ እ.አ.አ. 1904 የአሜሪካን መንግሥት ከፈረንሳይ መንግሥት ጋር በመስማማት ግንባታውን ለማስቀጠል ወስኖ የግንባታውን መሀንዲስ በመቀየር እና ዲዛይኑን በመከለስ ወደሥራ ገባ።

በፕሮጀክቱ ስፍራም አዲስ የጤና ማዕከል ተቋቋመ፤ በዚህም ቀድሞ የነበረውን የወባ ስርጭትና የሠራተኞችን ሞት መቀነስ ተችሏል።

በዚህ መልኩ እንደገና የተጀመረው የፓናማ ካናል ሥራ ተጨማሪ ከአስር ዓመታት የግንባታ ጊዜ ከወሰደ በኋላ እ.አ.አ. 1914 ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ለመርከቦች ክፍት ሆነ። ወሳኙ ፕሮጀክትም በፈረንሳይ ተጀምሮ በአሜሪካን ተጠናቀቀ።

አሜሪካም የፓናማ ካናል ባለቤት ሆና እስከ አውሮፓውያኑ 1999 ድረስ ካናሉን ስታስተዳድር ቆይታለች። በፓናማ መንግሥት በኩል ካናሉን ለማስተዳደር በነበረው የረጅም ጊዜ የይገባኛል ጥያቄ መሰረትም ባለቤትነቱ ወደ ፓናማ ሪፐብሊክ ተዛውሮ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እየተደረገለት ለዓለም አቀፍ መርከቦች አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

በተለያዩ ምክንያቶች ተጀምሮ እየተቋረጠ በብዙ ሺህ ሠራተኞች መስዋዕትነት ተከፍሎበት በአጠቃላይ በተጀመረ 33 ዓመቱ የተጠናቀቀው የፓናማ ካናል 13 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚረዝመውንና ሁለት ወራትን ይወስድ የነበረውን መንገድ ወደ 82 ኪሎ ሜትር ወይም አስር ሰዓታት ወደሚፈጅ ጉዞ ለመቀነስ ያስቻለ ነው።

ፕሮጀክቱ የሰው ልጅ የምህንድስና ብቃትን እና ከትውልድ ትውልድ የማይቋረጥ የዓላማ ጽናት የሚያስገኘውን ውጤት ማሳያ ሆኖም ይጠቀሳል።

 

በዋሲሁን ተስፋዬ