ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ’ዴሌቦ በቀድሞው በከንባታ እና ሐዲያ አውራጃ በኩፋላ ሐበሌ ግንቦት 12 ቀን 1930 ዓ.ም ተወልደው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በቢቾ ሆሣዕና ሚሽን ት/ቤት እና በመንግሥት ትምህርት ቤት ሲከታተሉ ቆይተው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አዳማ በሚገኘው በአጼ ገላውዴዎስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና ባይብል አካዳሚ ተምረዋል።
ከዚያም ወደ አሜሪካ በማቅናት በኮሙኒቲ ኮሌጅ የከፍተኛ ትምህርታቸውን ተከታትለው በኀብረተሰብ ታሪክ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ተቀብለዋል። ከሐዋርድ ዩኒቨርሲቲም በአፍሪካ ታሪክ ጥናት የማስተርስ ዲግሪያቸውን፣ በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ እና በአውሮፖ ታሪክና በፍልስፍና የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ ወስደዋል።
ዶክትሬታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ተሰጥቷቸው ለሁለት ዓመታት በቨርጂኒያ ዩንየን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ሲያስተምሩ ቆይተው አብዮቱ ሲፈነዳ ‘የታሪክ አካል መሆን አለብኝ’ በማለት ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተመልሰዋል። ያኔ የነበራቸውን ስሜት ሲገልፁ “የኢትዮጵያ አንድነትን እንደ ጣኦት እያመለኩት መጣሁ” ይላሉ።
ወደሀገራቸውም ተመልሰው በዚሁ ስሜትና ሀሳብ ዙሪያም ምርምራቸውን እና ማስተማሩን ገፍተውበት አገራቸውን ያገለገሉ ምሁር ናቸው።
በአሜሪካን ሀገር በፍልስፍና እና በታሪክ የመጀመሪያ ድግሪያቸውን ሲማሩ ከአምስት መቶ ተማሪዎች አንደኛ በመውጣት ከፍተኛ አድናቆት ማትረፍ ችለዋል። በዚህም ምክንያት በርካታ የአሜሪካን ሀገር ዩንቨርስቲዎች የነፃ የትምህርት ዕድል በአማራጭነት አቅርበውላቸዋል።
ፕሮፌሰር ላዺሶ ብዙ በተማሩበት ዘርፍ ባደረጉት ምርምር በርካታ የታሪክ መፃህፍትን ያሳተሙ ሲሆን ዐበይት በሆኑ ሀገራዊ የታሪክ ክስተቶችም ላይ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ማለትም በሬዲዮና በቴለቪዥን ላይ በመቅረብ ጠለቅ ያለ ትንተና በመስጠት ይታወቃሉ።
ፕሮፌሰር ላዺሶ ጌታሁን ድሌቦ ካሳተሟቸውም የታሪክ ስራዎች ውስጥ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡-
1. የኢትዮጵያ የገባር ሥርዓትና ጅምር ካፒታሊዝም፣ 1ኛና 2ኛ የታሪክ መጻሕፍት
2. የኢትዮጵያ ረጅም የሕዝብና የመንግሥት ታሪክ 1ኛ መጽሐፍ፣
3. የኢትዮጵያዊነት ታሪካዊ መሰረቶችና መሳሪያዎች (ታሪክ)
4. የቀይ ባሕርና የዓባይ ሸለቆ ሚና፣ የምፅዋ ሲምፖሲየም-1974
5. የኢትዮጵያ የመከራ ሥርዓትና የኤርትራ ጥያቄ፣ 1ኛ፣2ኛ እና 3ኛ መጽሐፍ
6. አጭር የጌዴኦ ህዝብ ታሪክ ከ1982-1966
7. የምርትና የባህል ዘመቻ በከንባታና ሀዲያ አውራጃ
8. የአዲስ አበባ መዲና እድገትና ሚና በኢትዮጵያ ታሪክ
9. ናሽናል አትላስ እና
10. ሌሎች በርካታ የታሪክ መጻሕፍት አሳትመው ለአንባብያን አቅርበዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት የራሳቸው ፍልስፍና (school of thought) እንዳለቸው የሚነገርላቸው ፕሮፌሰሩ፣ በዚህም አስተምህሯቸው ምክንያት ብዙ ፈታናዎችን እና ተቃውሞችን ማስተናገዳቸውን በተለያዩ ጊዚያት ከሰጡት ቃለ መጠይቆች ተደምጠዋል።
በባህሪያቸው ግልፅ፣ ታማኝ እና ሰው አክባሪ እንደሆኑ በባልደረቦቻቸው የሚመሰከርላቸው ፕሮፌሰር ላዺሶ፤ “ሰው ሁሉ አንድ ነው፤ ከአንድ ዘር ነው የመጣው፤ ሰውን ከሰው የሚለየው ስራው ነው” ይላሉ።
“የኢትዮጵያ ታሪክ የሁሉ ካልሆነ የማንም አይሆንም” የሚል መርህ እንዳለቸው የሚናገሩት ፕሮፌሰር ላዺሶ፤ የአንዱን ብሔር ወይም ሐይማኖት ታሪክ ነጥለን ከዚያ አንፃር ብቻ የኢትዮጵያን ታሪክ የምንጽፍ እና የምንተነትን ከሆነ ትክክለኛውን የኢትዮጵያ ታሪክ ማወቅ አንችልም ሲሉ ይገልፃሉ።
“የኢትዮጵያ ታሪክ የክርስትናው፣ የእስልምናው እና የሌሎች ኃይማኖቶች እንዲሁም የብዙ ቋንቋዎች እና ህዝቦች መስተጋብር ነው” በሚል ሙግታቸው ይታወቃሉ።
ባለትዳር እና የሦስት ሴት ልጆች አባት የነበሩት የታሪክ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ’ዴሌቦ፤ ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው በዛሬው ዕለት በ87 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
የፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ’ዴሌቦ የአስክሬን ሽኝትና ቀብር ሥነ ሥርዓት የፊታችን ማክሰኛ ሕዳር 2 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚከናወን ተገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የፕሮፌሰር ላጲሶ ጌ’ዴሌቦ ህልፈትን አስመልክቶ ባስተላለፉት የሀዘን መግለጫ መልዕክት፤ አንጋፋው የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር ላዺሶ ጌ. ዴሌቦ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ዛሬ ማለፋቸውን በታላቅ ኀዘን መስማታቸውን ገልጸው፤ ነፍሳቸውን በዐጸደ ገነት እንዲያኖርና እና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን እንዲሰጥ እመኛለሁ ብለዋል።