ከ1950ዎቹ ጀምሮ በኢትዮጵያ ባሕር ኃይል ውስጥ ሀገራቸውን ሲያገለግሉ የነበሩ የቀድሞ አባላቱ፣ ዛሬ ላይ በክበባቸው አዘውትረው ይገናኛሉ፡፡
የቀድሞ የባሕር ኃይል ዓባላቱ የባሕር ላይ ቆይታቸውን ሲያስታውሱም፣ በመካከላቸው የነበረው አብሮነት ቤተሰባዊ እና ኢትዮጵያዊነት የሰፈነበት እንደነበር ያነሳሉ፡፡
ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት የነበረችበት ወቅት ‘ወርቃማው ዘመን’ ነበር የሚሉት አባላቱ፤ ኢትዮጵያን ያለ ባሕር በር ማሰብ አይቻለንም ይላሉ፡፡

ኢትዮጵያ በወቅቱ የነበራትን ኃያልነት እና የንግድ እንቅስቃሴ በትዝታ እንደሚያስታውሱት በመግለፅም፣ የባሕር በር ባለቤት አለመሆን የሚያስከፍለውን ዋጋ ለመመስከር ቀዳሚ እማኞች እኛ ነን ሲሉ ይናገራሉ፡፡
ኢትዮጵያ በባሕር ላይ የነበራት እንቅስቃሴ ለቀጠናው ሰላም እና መረጋጋት፣ ለዜጎች ገቢ መሻሻል፣ ለተረጋጋ የሸቀጦች ዋጋና የንግድ እንቅስቃሴ እና መሰል ነጥቦች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አባላቱ ለኢቢሲ እሁድ ቤት ብታዩት መሰናዶ ገልጸዋል፡፡

ባሕር ላይ በነበረን የሥራ ቆይታ የሀገርን ኢኮኖሚ ከመደገፍ ባለፈ የራሳችንን ኑሮ ያበጀንበት ነው ሲሉ ይገልጻሉ የቀድሞ የባሕር ኃይል አባላቱ፡፡
የሀገራችንን ዳር ድንበር በየዕለቱ በመቃኘትም ሉዓላዊነቷ የተከበረ ኃያል ሀገር ሆና እንድትቀጥል የባሕር ላይ ቆይታችን አስችሎናል ብለዋል፡፡
ያጣነውን የባሕር በር ባለቤትነት ለማስመለስ የተጀመረው የተጠቃሚነት ጥያቄ በሙሉ አቅም መቀጠል እንዳለበት በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡
በአፎሚያ ክበበው